መንግሥት ሱዳን ከጠብ አጫሪ ድርጊቷ እንድትቆጠብ ጠየቀ

ሰኔ 20/2014 (ዋልታ) መንግሥት የሱዳን መከላከያ በድንበር አካባቢ ያለውን ውጥረት ምክንያት በማድረግ እያደረገ ካለው ትንኮሳ እንዲቆጠብ ጠየቀ፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ድጋፍ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በገቡ የሱዳን መደበኛ ወታደሮች ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው መንግሥት በኢትየጵያ እና ሱዳን አዋሳኝ ድንበር መካከል የተከሰተውን አሳዛኝ ክስተት መገንዘቡን አስታውቋል፡፡

ድርጊቱ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የተፈጸመው በአሸባሪው የሕወሓት አባላት የሚደገፈው የሱዳን መደበኛ ጦር ሠራዊት የኢትዮጰያን መሬት ከወረረ በኋላ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት ፀብ ጫሪ ድርጊት የፈፀመው ወገን የሱዳን ጦር ሆኖ ሳለ በሁኔታው ኢትዮጵያን ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞከርን የትኛውንም ድርጊት ግን አልቀበልም ብሏል።

መንግሥት ይህ ኢትዮጵያን ከጀመረችው የሰላም እና የዕድገት ጎዳና ለማደናቀፍ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነውና በጉዳዩ ላይ ምርመራ አካሂዳለው ብሏል፡፡

የሱዳን መንግሥት ሁኔታዎችን ከማባባስ እንዲቆጠብ የጠየቀ ሲሆን ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጧል፡፡