መንግሥት በሶማሌ ክልል በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቆመ

የካቲት 23/2014 (ዋልታ) መንግሥት በሶማሌ ክልል በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ፡፡

በሚኒስትሩ የተመራ ከፍተኛ የመንግሥት የልዑካን ቡድን በሶማሌ ክልል በድርቅ ምክንያት ከአምስት ዞኖች ተፈናቅለው በፋፈን ዞን ወደ ሐሮሬስ ወረዳ የሰፈሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ጎብኝተዋል።

የቤት እንስሳትን ይዘው በሐሮሬስ ወረዳ የሚገኙት የድርቅ ተፈናቃዮች በአሁኑ ወቅት ያሉበትን ሁኔታ የገለፁላቸው ሲሆን በዚህም የወረዳው ማኅበረሰብ ያለውን ውሃና የእንስሳት መኖ እየሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የተፈናቃዮች ቁጥርና ፍላጎት ከወረዳው አቅም በላይ በመሆኑ መንግሥት የውሃና የመኖ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሶማሌ ክልል ድርቁ በስፋት የተከሰተ እንደመሆኑ በክልሉ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችንና እንስሳቱን ለመታደግ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በድርቁ ምክንያት የሰው ህይወት እንዳይጠፋ እየተሰራ መሆኑን መጥቀሳቸውን ከሶማሌ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።