መንግሥት ልዩ መልዕክተኞች እና አምባሳደሮች ወደ መቀለ የደርሶ መልስ ጉዞ እንዲያደርጉ ፈቅዷል – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

ሐምሌ 21/2014 (ዋልታ) መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞች ወደ መቀለ የደርሶ መልስ ጉዞ እንዲያደርጉ የፈቀደላቸው መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ።

ከልዩ መልዕክተኞቹ በተጨማሪ ለአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና እንግሊዝ አምባሳደሮች ፍቃድ መስጠቱን ጠቁመዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና ፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሞያተኞች ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ያለው ልዩነት እንዲጠብ እና የሚያስማማ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ለልዩ መልዕክተኞች እና ለአምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ዙሪያ ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ለሰላም ውይይት ዝግጁ መሆኑን ለተባበሩት መንግስታት፣ ለአውሮፓ ኅብረት እና ለአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞች ማብራራታቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም መንግሥት በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ለሰላም ውይይት ዝግጁ መሆኑን እና ውይይቱ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ መጀመር አለበት የሚል አቋም ያለው መሆኑን ማብራራታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የውይይት ሂደቱን እንዲመራ እና ከየትኛውም ምንጭ የሚገኘውን ሎጂስቲክስ እንዲያሳልጥ የመንግሥት ፍላጎት መሆኑንም አምባሳደሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባጋሩት መረጃ አመላክተዋል፡፡