መንግሥት አምነስቲና ሂውማን ራይት ዎች እውነቱን ማወቅ ከፈለጉ በጥልቁ እንዲመረምሩ መከረ

መጋቢት 29/2014 (ዋልታ) አምነስቲና ሂውማን ራይት ዎች በሰሞነኛ ሪፖርታቸው በሃሰት ባቀናበሩት ድርሰት ዓለምን ከማሳሳት ይልቅ እውነቱን ሊመረምሩ እንደሚገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከሰሞኑ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት በአሸባሪው ትሕነግ የግፍ አገዛዝ ዓመታት የተፈፀሙ የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ማሳያዎችን ማውጣቱ ይታወቃል።

ይህ መረጃ በወጣ ማግስት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች በለመዱት አግባብ ዓለም ዐቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳሳት በማለም ሀሰት ላይ የተመሰረተ ሪፖርት ማውጣታቸው ይታወሳል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጎንደር ላይ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫቸው በሳምንቱ ከተከናወኑ የዲፕሎማሲ ተግባራት ባሻገር ሁለቱ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ባወጡትና የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግሥትና ሕዝብን ወንጀለኛ ለማድረግ የሞከሩበትን ሴራ በተመለከተ አብራርተዋል።

ተቋማቱ የሽብር ቡድኑ ትሕነግ ማንነትን መሰረት አድርጎ ግፍ ሲፈፅምባቸው በኖረባቸው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም አካባቢው የትግራይ ተወላጆች በፌደራልና በአማራ ክልል መንግሥታትና ሕዝብ ዘር ተኮር በደል እየተፈፀመባቸው እንደሆነ በመጥቀስ በአካባቢዎቹ ዓለም ዐቀፍ የሰላም አስከባሪ ይሰማራ እስከማለት ደርሰዋል።

ይህ ሪፖርት የወጣው ደግሞ ትሕነግ ለ30 በላይ ዓመታት በአካባቢዎቹ በአማራነታቸው እየለየ በግፍ የጨፈጨፋቸው ንፁሃን ከ12 በላይ የጅምላ መቃብሮች መገኘቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ መሆኑም የእነ አምነስቲን ፍላጎት የአሸባሪውን ትሕነግን ወንጀል መሸፈን እንደሆነ ጠቋሚ ነው።

አምባሳደር ዲና ተቋማቱ በጭፍኑ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናትን ለማጣጣል ከመሞከር ይልቅ እውነቱን ማጥራት ላይ ቢያተኩሩ እንደሚበጃቸው አንስተው አሁን ያወጡት ሪፖርት ተቀባይነት የለውም ብለዋል። እውነቱን ለማወቅ ከፈለጉ ግን መንግሥት እገዛ እንደሚያደርግ ነው የገለፁት።

ከኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ጋር በተያያዘ በተመደበው በኢትዮጵያ የኤርትራ ጉዳይ አስፈፃሚ የሁለቱን አገራት ግንኙነት መገምገም አይቻልምም ነው ያሉት።

በአሜሪካ በኩል የተረቀቁት HR 6600 እና S3199 ለጊዜው እንዲገታ ተደርጓል የሚለውን መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳላረጋገጠና አሁንም ሂደት ላይ እንደሆኑ አምኖ ሳይዘናጉ ዲፕሎማሲው ላይ መጠንከርን ምርጫው እንዳደረገ ቃል አቀባዩ አሳውቀዋል።

ስንታየሁ አባተ (ከጎንደር)