መንግሥት አገርን ለማፍረስ በትጥቅ ከሚታገሉ ኃይሎች ጋር ሥልጣን የምጋራበትና የምደራደርበት መንገድ የለም አለ

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) መንግሥት በኢትዮጵያ ጦርነት ከፍቶ በርካታ የጦር ወንጀሎችን እየፈፀመ ካለው የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ጋር በድርድርና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ችግራችሁን ፍቱ ማለት መሬት ካለው እውነት ጋር መቃረን ነው አለ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ ሚኒስትር ዛዲግ አብርሃ በአልጀዚራ ኢንሳይድ ስቶሪ ላይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ የሽብር ቡድኑ ከተሞችን መደብደብና ንፁሃንን በጅምላ መግደልን ጨምሮ የተለያዩ የጦር ወንጀሎችን እየፈፀመ እንዳለ አስታውሰዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ሕወሓትና ጀሌዎቹ ወደአዲስ አበባ እየቀረብን ነው ሲሉ የሚያሰራጩት ሁሉ ቅዠት መሆኑንም ያሳወቁ ሲሆን፤ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መዝመታቸውን ተከትሎ የወገን ጦር ሞራል በከፍተኛ ደረጃ መነቃቃቱን አክለዋል፡፡
በዚህም ነገሮች በፍጥነት እየተቀለበሱና የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ የጦር መሪዎች እየተደመሰሱ ነው ብለዋል፡፡
እየተዋጋን ያለነው የአገራችንን ሉኣላዊነትና የግዛት አንድነት ለመታደግ እንደሆነ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ መረዳት አለበት ያሉት ሚኒስትሩ ታሪክና ጊዜው ከእኛ ጋር ነው ሲሉም የኢትዮጵያን አሸናፊነት መቅረብ ግልፅ አድርገዋል፡፡
‹የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ማዕከላዊ ሥልጣንን ለማጥበቅ ሲል ዴሞክራሲን አፍኗል› በሚል ለሚነሳው ወቀሳ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትር ዛዲግ ‹‹ይሄ ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው›› ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ አሁን ያለው መንግሥት በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታትን ጨምሮ አሳሪ ሕጎችን ያሻሻለ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
መንግሥት በምርጫ 97 ነጥብ 8 በመቶ የፓርላማ መቀመጫን ቢያሸንፍም ከወረዳ እስከ ፌደራል ካቢኔ ባለው እርከን ሥልጣኑን ለበርካታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያጋራ ቁርጠኛ የዴሞክራሲ ደጋፊ መሆኑን ነው ለአብነት የጠቀሱት፡፡
‹መንግሥት በትጥቅ ከሚታሉ ጋር የሥልጣን መጋራት ሐሳብ የለውም ወይ› ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዛዲግ ‹‹ኢትዮጵያን ፍጹም ፈላጭ ቆራጭ ወደሆነ አገዛዝ የሚመልስ በመሆኑ የማይታሰብ ነው›› ሲሉ ለጠላትም ለወዳጅም ቁርጡን አሳውቀዋል፡፡ መንግሥት ዜጎችን ከሚገድልና ከተማ ከሚያጠፋ አካል ጋር ሥልጣን የሚጋራበት እሳቤ አይኖርም ነው ያሉት፡፡