መንግሥት ከሰብአዊ የእርዳታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሰብአዊ እርዳታ የሚደርስባቸውን መንገዶች እያስፋፋ ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ጥቅምት 8/2015 (ዋልታ) የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትንና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ስለማስቀጠል የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተወሰኑ የትግራይ ክልል ከተሞችን መቆጣጠሩ ይታወቃል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከተሞች የጦርነት ቦታ እንዳይሆኑ የሚያደርግ የጥንቃቄ አካሄድ እንደሚከተል መግለጹ ይታወሳል።

የመከላከያ ሠራዊት በከተሞች ጦርነት እንዳይደረግ የተከተለው ጥብቅ ዲሲፕሊን፣ በሲቪሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አድርጓል።

የኢትዮጵያ መከላከያ በከተሞች ውስጥ ምንም ዓይነት ጦርነት ሳያካሂድ ሽሬን፣ አላማጣና ኮረም ከተሞችን ለመቆጣጠር ችሏል። ይህ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተከተለው ጥብቅ ወታደራዊ ዲሲፕሊን፣ የሕወሐትን ፕሮፓጋንዳ ሲያስተጋቡ የነበሩ አካላትን ሟርት ያመከነ ነው።

ከልዩ ልዩ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት፣ መከላከያ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች እርዳታ በተሣለጠ መንገድ እንዲደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት በቂ ዝግጅት አድርጓል። ይሄም የሽሬ አውሮፕላን ማረፊያን ተጠቅሞ እርዳታ ማድረስን ይጨምራል።

መንግሥት ከሰብአዊ የእርዳታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሰብአዊ እርዳታ የሚደርስባቸውን መንገዶች እያስፋፋ ነው። በተቀናጀ መንገድ በሰሜን ጎንደር በኩል ወደ ሽሬ የሚወስደውን እና ከኮምቦልቻ – ደሴ- ወልድያ- ቆቦ- አላማጣ ያለውን መንገድ ለመክፈት እየሠራ ነው። ይሄንን ሥራ የሚያሣልጥ ኮሚቴ ከሚመለከታቸው አካላት ተወጣጥቶ ሥራ ጀምሯል።

እነዚህ ሥራዎች ቴክኒካዊ የሆኑ ጥናቶችን እና ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥራዎችን ይጨምራል።

ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!