መስከረም 14/2014 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኒውዮርክ ቆይታቸው ከተባበሩት መንግሥታት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና ጄኔ መሐመድ ጋር መክረዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እና የወደሙ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባት መንግሥት በላቀ አጋርነት ከተመድ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ገልፀውላቸዋል።
በዘላቂ ልማት ግቦች አፈፃፀም፣ በሰብኣዊ አገልግሎት ድጋፍ አሰጣጥ እና ወቅታዊ የሃገር ውስጥ ጉዳዮችን በተመለከተ በዝርዝር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም እና በአሸባሪው ሕወሓት የወደሙ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ደመቀ ተናግረዋል።
በመሆኑም መንግስት በመልሶ ማቋቋም እና በመልሶ ማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሂደት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በላቀ አጋርነት ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል።
በአሁን ጊዜ ሃገራችንን እየገጠሟት ካሉት የፀጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ የመልሶ ማቋቋም እና የመልሶ ማልማት ተልዕኮን ለማስፈፀም በመንግሥታቱ በኩል የበለጠ ትብብር እና ድጋፍ እንጠብቃለንም ብለዋል።
እስካሁን ድረስ የተባበሩት መንግሥታት በልማት እና ሰብኣዊ ድጋፍ አገልግሎት ዙሪያ ለኢትዮጵያ ላበረከተው አስተዋፅዖ በማመስገን፤ ጊዜው የተሻለ ትብብርና መደጋገፍ እንደሚጠይቅ ማስገንዘባቸውንም ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።