መንግሥት ወደ ትግራይ ላለመግባት ያሳለፈው ውሳኔ ኳሱ ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ሕወሓት ሜዳ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል – ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን

ታኅሣሥ 23/2014 (ዋልታ) መንግሥት ወደ ትግራይ አልገባም ብሎ ያሳለፈው ውሳኔ ችግሩን ከጦርነት ውጭ ለመፍታት ኳሱ ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ሕወሓት ሜዳ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ የሚፈፀመውን ወታደራዊ ዕርምጃ ላለመቀጠል መወሰኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ውሳኔው ከጦርነት ውጪ ያሉ ሌሎች የመፍትሄ አማራጮችን ለማጤን ዕድል የሚከፍት በመሆኑ ብዙዎች በደስታ ተቀብለውታል፤ አሁን ኳሱ ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ሕወሓት አደባባይ ነው ሲሉም ሁኔታውን አስረድተዋል።

አሜሪካ ግን ከዚህ የኢትዮጵያ አካሄድ በተቃራኒው መቆሟን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለሚደርስባት ግፊት አልንበረከክም በማለቷ የአሜሪካን አስተዳደር የሚያደርስባት ጫና መበርታቱንም አስረድተዋል፡፡ በዚህም የአሜሪካ መንግሥት አንዳንድ የችኮላ ውሳኔዎችን ወስኗል፤ በዚህም እናዝናለን ብለዋል።

የአሜሪካ አስተዳደርና የህግ አውጭ አካላት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ላይ በሚጥሏቸው ማዕቀቦችንና ዕርምጃዎች ከፍተኛ ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያውያን አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን በቃህ ካሉት ቆይተዋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ የዓለም ማኀበረሰብ ይህንን በአግባቡ ቢረዳ ኖሮ ይህ ሁሉ ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻዎች በኢትዮጵያ ላይ አይፈጠሩም ነበር ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ያለውን አቋም እንደገና እንዲያድስና እንዲመለከት ጥብቅ በሆኑና በማያሻማ መልኩ ኢተዮጵያ ታሳስባለች ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የፈረንጆቹን 2022 አዲስ ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው የኅልውናና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ዘመቻ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ከመቼውም ጊዜ ከፍ ባለ ሁኔታ እንዳጠናከረው አንስተዋል።

ከአገር ውስጥ ባለፈ ኢትዮጵያ ከተለያየ አቅጣጫዎች ድጋፍ እንደነበራት አንስተው ጫናዎች በበዙበት ወቅት ኢትዮጵያ ጠንካራ ወዳጆችንም አግኝታለች። ኢትዮጵያም ለእነዚህ የአፍሪካና በሌሎች ክፍላተ ዓለም ለሚገኙ ወዳጅ አገራት ለህልውናችን ለምናደርገውን ትግል ለሰጡት የማያቋርጥ ድጋፍ ታመሰግናለች ብለዋል።

በተጨማሪ ከተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የተውጣጡ ሰዎች ኢትዮጵያን ለመደገፍ ዓለም ዐቀፉን የ #Nomore እንቅስቃሴን ሲቀላቀሉ ማየትም ልብን የሚያሞቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን ያለው ትውልድ በቀደምት አባቶቹና በአያቶቹ የጀግንነት ታሪክ የሚኮራበትን ያህል፣ ሌሎች ሊያስብባቸው የሚገቡ ጉዳዮችም አሉበት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተለይም ሃሳብን መግለጽና ለመግባባት የሚረዱ የማያቋርጡ ውይይቶች የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።

በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ መንግሥት ሁኔታዎችን በተቻለ ፍጥነት የማመቻቸትና የመምራት ታሪካዊ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበትም ገልጸዋል። ለአገራዊ ምክክሩ የሚረዳ አስፈላጊው መሠረት ተቀምጦ ምክክሩ በቅርቡ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ዋና ዋና ልዩነቶቻችችን ለመፍታት የሚረዳው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ውይይት ኮሚሽንም ማቋቋሚያ አዋጅ ፀድቋል።

የኮሚሽኑ አላማ በጋራ ታሪካችን ላይ የጋራ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ፣ አሁን ላለንበትና በትውልዶች መካከል ላሉት ተግዳሮቶች የጋራ መፍትሄዎችን ለመፈለግ እንዲሁም የቀጣይ መንገዳችንን ለመቅረጽ የሚረዳ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ አሁን የተፈናቀሉ ዜጎቿን መልሶ የማቋቋም፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባትና የማደስ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እያደረገች ነው። በዚህም ለዜጎች አገልግሎቶች መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመልዕክታቸው ማስተላለፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡