መንግሥት የመልሶ ግንባታ እና የበጋ መስኖ ሥራዎች በተሟላ መልኩ እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታወቀ

ጥር 19/2014 (ዋልታ) የመልሶ ግንባታ እና የበጋ መስኖ ሥራዎች በተሟላ መልኩ እየተከናወኑ መሆናቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም አሸባሪው ሕወሓት በነበረባቸው አካባቢዎች የመስኖ ሥራው ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በንቅናቄ የተፋሰስ ሥራዎች እንዲሰሩ የታወጀ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎችም ተጀምሯልም ነው የተባለው፡፡

የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ክልሎች እያደረጉት ያለው ድጋፍና አጋርነት የሚበረታታ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በሶማሌ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት ከክልል መንግሥታት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነና የእለት ደራሽ እርዳታም እየተሰጠ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የአስቸኳይ አዋጁን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ አዋጁን ከስድስት ወር በፊት ማንሳት አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘ ገልጸው የአሸባሪው ተላላኪዎች ንጹሃን መስለው በተለያዩ ከተሞች ሲያደርጉት የነበረውን ተግባር ለመቆጣጠር የአስቸኳይ አዋጅ አስፈልጎ ነበር ብለዋል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትብብር ባደረገው ተጋድሎ የአሸባሪው ህልም በመክሸፉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት ግድ ሆኗል ሲሉም አክለዋል፡፡

በተለይ ደግሞ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር አሁን ላይ ተገድቧል ያሉት ሚኒስትሩ አዋጅ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ስለሚነካ ሰላም በሰፈነበት ጊዜ አያስፈልግም ብለዋል፡፡