መንግሥት የሚያደርገው የነዳጅ ድጎማ ለ132 ቢሊየን ብር የእዳ ክምችት እንዳጋለጠው ገለጸ

ግንቦት 24/2014 (ዋልታ) መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገው ድጎማ ኢትዮጵያን ለ132 ቢሊየን ብር የእዳ ክምችት እንድትጋለጥ ማድረጉ ተገለጸ።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የነዳጅ ድጎማ ማስተካከያ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫናን በማይፈጥር መልኩ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገው ድጎማ  ለ132 ቢሊየን ብር የእዳ ክምችት እንድትጋለጥ ማድረጉ ነው የገለጸው።

በባልሥልጣኑ የነዳጅ ውጤቶች ግብይት ስታንዳርድ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር  ለገሰ ቱሉ ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤቶቿ ሁሉ ነዳጅን በውጭ ምንዛሬ ግብይት እንደምትገዛ አስታውቋል።

ነዳጁ አገር ውስጥ ከገባ በኋላም ከተገዛበት ዋጋ በግማሽ ባነሰ ገንዘብ ለግብይት እንደሚቀርብ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ግብይቱም መንግሥት በሚከተለው የድጎማ አሰራር መሰረት እንደ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ሶማሊያ ያሉ  ጎረቤት አገራት ጋር ሲነፃጸር በግማሽ ያነሰና ሰፊ የዋጋ ልዩነት እንዲኖረው  አድርጎታል ብለዋል።

ዓለም ዐቀፉን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪና መንግሥትም የዋጋ ማስተካከያ ሊያደርግ ይችላል በሚል ነዳጅን በማስቀመጥ እጥረት እንዲከሰት በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አገርን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኘውን የነዳጅ ግብይት ወጥ ለማድረግም መንግሥት የነዳጅ ግብይትና ሥርጭት ማስተካከያ ማድረጉ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።