ነሃሴ 4/2013 (ዋልታ) – መንግሥት የትግል ስልቱን አሸባሪውን ቡድን ሊያጠፋ በሚችል መልኩ መቀየሱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ዳይሬክተር ጀነራሉ እንዳሉት አሸባሪው የትህነግ ቡድን የመንግሥትን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአማራና በአፋር ክልሎች ግልጽ ወረራ አድርጓል፡፡
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሕዝብ በደርግ መንግሥት ላይ ያለውን ጥላቻ በመጠቀም ‹‹ከደርግ ጋር እንጂ ከሕዝብ ጋር ጠብ የለኝም›› በማለቱ ድጋፍ አግኝቶ ነበር ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሳይውል ሳያድር የበደል ክንዱን በሕዝብ ላይ ሲያሳርፍ ዓመታትን እንዳሳለፈ ገልጸው አሁንም እንደለመደው ችግሬ ከሕዝብ ሳይሆን ከመንግሥት ጋር ነው በማለት ጉዳዩን ከአማራ ልሂቃን፣ ከአማራ ልዩ ኀይልና ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ለማያያዝ ሙከራ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ሆኖም በደረሰባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማትን፣ ትምሕርት ቤቶችን፣ የመብራት፣ የስልክ እና የመንገድ መሠረተ ልማቶችን እያወደመ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
ግለሰቦችን የመግደል፣ የማፈናቀልና የሕዝብን ሀብት የመዝረፍና ሌሎች የሽብር ድርጊቶችንም እየፈጸመ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የሕዝብ ሀብት እያወደሙና እየዘረፉ ከሕዝብ ጋር ጠብ የለኝም ማለት ተቀባይነት እንደሌለው ያነሱት አቶ ተመሥገን ሕዝቡም በሁኔታው መማረሩን ጠቅሰዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚያደርገው ጥረት በተለይ የአማራ ሕዝብን የማዳከም ስትራቴጂ መንደፉ ይታወቃል፡፡
በዚህ ድርጊቱ የቀጠለው የሽብር ቡድን ሕዝቡ በደስታ ተቀብሎናል ማለቱ አሳፋሪ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ሕዝቡ በየአካባቢው ለወገን ጦር ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ ሰርጎ ገቦችን እየመከተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ሕዝቡ የአሸባሪውን ቡድን አባላት እያሳደደ ብሬን፣ ዲሽቃ፣ መትረየስ እና ክላሽ ማርኳል፤ ምርኮኞችንም ለመንግሥት እያስረከበ ነው ብለዋል።
የወርቄ፣ ጎብዬና የሀራ ሚሊሻዎች ከሰሞኑ ታሪካዊ ገድል እየሠሩ መሆኑንም ጠቁመው የጋይንት ሚሊሻ፣ ሕዝብ እና ፋኖ በጥምረት ታሪክ ሠርተዋል ብለዋል፡፡
የቆቦ ወጣቶችም በተለያዩ አካባቢዎች እስካሁን እየተፋለሙ እንደሆነም ገልጸዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡
“የአማራ ሕዝብ የሚዘርፈውን ኀይል የሚቀበል አይደለም” ያሉት አቶ ተመሥገን ወራሪው፣ ተስፋፊውና አሸባሪው ቡድን ከሚነዛው የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በተቃራኒ ሕዝብ እየተፋለመው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥትም የትግሉን ስልት አሸባሪውን ሊያጠፋ በሚችል መልኩ ቀይሷል ብለዋል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ ወታደራዊ ስልጠና እየተሰጠ ሲሆን የአሸባሪውን ቡድን በማስወገድ የሕዝቡን ነጻነት እናረጋግጣለን ነው ያሉት፡፡
ይህ ቡድን በከፋፋይ አጀንዳ ኢትዮጵያን ለምስቅልቅል የዳረገ እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ያውቁታል ብለዋል፡፡
አቶ ተመሥገን በእኩይ ድርጊቱ በሕዝብ ትግል ከስልጣን እንደተወገደ ኹሉ በሕዝብ ትግል እንቀብረዋለን ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የነበረው ዓለም አቀፍ ጫና የሚታወቅ ነው ያሉት አቶ ተመሥገን ረድዔት ድርጅቶች፣ በእርዳታ ስም የተደራጁ ነገር ግን ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ መንግሥትን በመተቸት ሲረባረቡ ቆይተዋል፤ አሁንም እየተረባረቡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
መንግሥት ያደረገውን ሰብዓዊ ድጋፍ ከማጣጣል ጀምሮ ሠራዊቱ ድጋፍ እንዳይገባ ጫና አሳድሯል የሚል ጩኸት ማሰማታቸውም የቅርብ ጊዜ ኹነት እንደኾነ አብራርተዋል፡፡
ሚዛናዊነት የጎደለው የዘገባ ሽፋን የሚሰጡ በርካታ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት እንዳሉም አቶ ተመስገን ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ሀገር ሲመራ በነበረባቸው ጊዜያት የዘረጋውን ዓለም አቀፍ መረብና ተላላኪዎቹን በመጠቀም በመንግሥት ላይ ጫና ለማድረስ ዘመቻ መከፈቱንም ነው ያስረዱት፡፡
አሸባሪው ቡድን ዓለም አቀፍ ሕግን ተላልፎ ሕጻናትን ለጦርነት ሲያሰልፍ፣ የጦር ወንጀሎችን ሲፈጽም፣ ወደ አጎራባች ክልሎች ወረራ ሲፈጽም፣ ንጹኃን ሰዎችን በጅምላ ሲጨፈጭፍ የኮነነው ዓለም አቀፍ ተቋም አለመኖሩንም አስታውሰዋል፡፡
የሚፈጽመው አሳፋሪ ተግባር መወገዝ እያለበት ሲያወድሱት ተስተውለዋል ነው ያሉት፡፡
‹‹አሸባሪውን ቡድን ማጥቃትና ማጥፋት ስንጀምር ዓለም አቀፍ ጩኸቱ እንዴት እንደሚሆን የምናየው ይሆናል›› ብለዋል፡፡
የሚነዛው የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ከሀገር ሕልውና የሚበልጥ አይደለም የሚሉት አቶ ተመሥገን ይህ ኀይል በሙሉ አቅም እና በመተጋገዝ ከምድረ ገጽ እንደሚጠፋ አስረድተዋል፡፡
በአፋር ክልል በተቀናጀ አግባብ ሕዝቡ ትግል እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ተመሥገን የአማራ ሕዝብ የጀመረውን ትግል በማጠናከርም ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ መፋለም ይገባዋል፤ መላው ኢትዮጵያውያንም የሕዝብ ጠላት የሆነውን የሽብር ቡድን ለማክሰም በሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡