መንግሥት የአትሌቶች አኩሪ ድል የኢትዮጵያዊያን የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ትውልድ ተሸጋሪ እሴት መሆኑን ያሳያል አለ

ነሐሴ 7/2014 (ዋልታ) በወጣት አትሌቶቻችን የተደገመው አኩሪ ድል የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ትውልድ ተሸጋሪ እሴት መሆኑን ያሳያል ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን አኩሪ ድል ማስመዝገባቸውን አስመልክቶ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

አገልግሎቱ በመልዕክቱም ድሉ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ትውልድ ተሸጋሪ የኢትዮጵያውያን መለያ እሴት ስለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው፤ድል ማድረግ ብሎም ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ከፍ ማድረግ የአትሌቶቻችን መታወቂያ ነው ሲል አውስቷል፡፡

በዚህ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ወጣት አትሌቶቻችን በአንድ ሰዓት ውስጥ ብቻ 5 የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፈው ዓለምን አስደምመዋል ያለው አገልግሎቱ በውድድሩ በአጠቃላይ 6 ወርቅ፣ 5 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳሊያ መገኘቱን ጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም እምብዛም ውጤት አምጥታባቸው በማታውቀው የ1 ሺሕ 500 እና 800 ሜትር እንዲሁም የመሰናክል ውድድሮች ሳይቀር የወርቅ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል፤ ይህም ኢትዮጵያ ያላትን የአትሌቲክስ እምቅ አቅም ከማሳየት አልፎ የአትሌቶቻችን የአሸናፊነት ስነልቦና የላቀ እንደሆነ ያመለክታል ነው ያለው፡፡

ወጣት አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ሀገር መሆኗን ለዓለም ማህበረሰብ ያሳየ እንደነበር እና ኢትዮጵያ የመቻል አቅሟ የት ድረስ እንደሆነ ተተኪ ባለድል ትውልድ ያላት ጠንካራ ሀገር መሆኗን እንደሚጠቁምም አስገንዝቧል፡፡

አገልግሎቱ  ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥም ሆና ስኬትን የምታስመዘግብ፣ የማትሰበር ሀገር መሆኗን ወጣት አትሌቶቻችን ለዓለም ማሳየታቸውን ነው የገለጸው፡፡

ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትሸነፍ፣ህብረብሔራዊ አንድነት በየዕለቱ የሚያፀናት እና የሚያንፃት ሀገር እንደሆነች በኮሎምቢያ ካሊ ከተማ በተግባር  መታየቱን አንስቷል፡፡

በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው 19ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡