መንግሥት የዘር ማጥፋት ወንጀል አልፈፀመም – ዓለም ዐቀፍ ሪፖርት

ጥቅምት 24/2014 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ መገናኛ ብዙኃንና መንግሥታት በኩል እየቀረበበት ያለውን ‹በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሟል› ክስ ዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽኖች የጋራ ምርመራ ሪፖርት ውድቅ አደረገው፡፡

የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ደጋፊ የሆኑ ምዕራባዊያን መንግሥታትና ድርጅቶች እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን ከአጋራቸው ሕወሓት ብቻ በሚወስዱት ሀሰተኛ መረጃ መንግሥት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሟል ሲሉ ቢከርሙም ሪፖርቱ መሰረተ ቢስ ሲል ውድቅ አድርጎታል፡፡

የጋራ ምርመራ ሪፖርቱ የተሰራው በኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጥምረት ነው፡፡

በተጨማሪም መንግሥት በተደጋጋሚ ሲከሰስባቸው የነበሩ እንደ ጾታዊ ጥቃትንና ረሃብን ለጦርነት ዓላማ መጠቀም ክስም በሪፖርቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡

ይልቁንም ሪፖርቱ ‹‹የትግራይ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ›› ሲል የገለፃቸው የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ስር የዋሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን እንዲሁም ሌሎች ንፁሃንን ብሔርን መሰረት ባደረገ መልኩ ጥቃት መፈጸማቸውንም አረጋግጧል፡፡

ይህም እስከዛሬ ያልተገለጹ የሽብር ቡድኑን ብዙ ጥፋቶች የሚያሳይና መንግሥት ሲያቀርባቸው የነበሩ መረጃዎችን ተዓማኒነት የሚያሳድጉ ሆነዋል፡፡