መንግስት ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነው

ሰኔ 27/2016 (አዲስ ዋልታ) መንግስት ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ነባር ችግሮችን በአገራዊ ምክክር እና ሽግግር ፍትህ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ነባር ችግሮች እና ወቅታዊ ስብራቶች ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ያደረጉ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ አኳያ በምክክሩ ነገን የተሻለ ለማድረግ የምንሰራበት ሲሆን ያለፉ በደሎችን ደግሞ በሽግግር ፍትህ የሚፈቱ ይሆናል ብለዋል፡፡

ወቅታዊ ችግሮች በተቋማት ሪፎርም እየተፈቱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ከዚህ አኳያ ለተመዘገቡ ስኬቶች እውቅና እየሰጠን የሚቀሩትን ደግሞ በጋራ መስራት አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

መፈንቅለ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሳካ የማይችል ኋላ ቀር እሳቤ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለረዥም ዘመናት በግጭትና ጦርነት አዙሪት ውስጥ አልፋለች ይህ የመገዳደል ታሪክ በእኛ ትውልድ ሊቆም ይገባል ነው ያሉት።

ባለፉት ጊዜያትም መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ በሆደ ሰፊነት በርካታ ርቀት ተጉዟል፤ በግጭትና ጦርነት ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን መያዝ ፈጽሞ አይቻልም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 36ኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ለኢትዮጵያ ዛሬም ነገም የሚበጀው በሰላምና በሰከነ መንገድ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት እንደሆነም ጠቁመዋል።