መንግስት በትግራይ ክልል የመልሶ ማቋቋም ትግበራ መጀመሩን ተከትሎ አልሚ ምግብና ሌሎች ሰብአዊ ድጋፎችን በማድረስ ላይ መሆኑን የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
በክልሉ አስቸኳይ የምግብና የሕክምና ቁሳቁስ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ካለፉት 10 ቀናት ጀምሮ በማቅረብ ላይ ነው።
በዚህም መሰረት የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በሽሬና ሌሎችም ከተሞች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ስንዴና አልሚ ምግብ እያቀረበ መሆኑ ተገልጿል።
በኮሚሽኑ የአደጋ ምላሽና ክትትል ቡድን መሪ አቶ ታዬ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሽሬ ከተማ ለተፈናቃዮች እየተሰጠ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ በሌሎች ከተሞችም ይቀጥላል።
ወደ ክልሉ ከተጓጓዘው ስንዴ ውስጥ ከ18 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ሽሬ ከተማ ደርሷል።
ይህም በሶስት ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች እየተከፋፋለ መሆኑን አቶ ታዬ ገልጸዋል።
“በተለይ ለእናቶች፣ ለህጻናት፣ ለሕሙማንና ለአረጋውያን የሚሆኑ አልሚ ምግቦችም እየተከፋፈሉ ነው” ብለዋል።
እየተደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ተፈናቃዮቹ በቀጣይ ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው ዘላቂ ህይወታቸውን እንዲጀምሩ መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።