መንግስት በየትኛውም አማራጭ ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ ይችላል-ሰላም ሚኒስቴር

ሐምሌ 29/2013 (ዋልታ) –  የህወሐት አሸባሪ ቡድን ስርአት የሚይዝ ከሆነ መንግስት በየትኛውም አማራጭ ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ ይችላል።

ለጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም ወቅት በትግራይ ክልል በተፈጠረው ሁኔታና የህወሐት አሸባሪ ቡድን እየፈጠረ ባለው ችግር ዙሪያ ለሃላፊዋ ሰፊ ገለፃና ማብራሪያ እንደተደረገላቸው የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።

ህወሐት በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ መሰየሙ ይታወሳል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የህወሐት አሸባሪ ቡድን እየፈፀመ ያለውን ጥፋት በትክክል እንዲረዱ ማስቻሉን ነው የጠቆሙት።

የህወሐት አሸባሪ ቡድን በአገር ላይ በፈጠረው የሀገር የህልውና አደጋ መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱንም እንዲረዱ ተደርጓል ብለዋል።

ሆኖም የህሐሃት አሸባሪ ቡድን በአገሪቱና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖርና ዜጎች ለችግር እንዲጋለጡ በጥፋት መንገድ መቀጠሉን አስረድተናቸዋል ብለዋል ወይዘሮ ሙፈሪያት።

ለተራድኦ ድርጅት ኃላፊዋ በተደረገላቸው ገለፃ የህወሃት አሸባሪ ቡድን ስርአት የሚይዝ ከሆነ መንግስት በየትኛውም አማራጭ ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚችል አረጋግጠውላቸዋል።

በትግራይ ክልል ለሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ በአግባቡ እንዳይደርስ አሸባሪ ቡድኑ እያስተጓጎለ መሆኑን ማስረዳታቸውን አመልክተው፤ ቡድኑ ከእኩይ አላማው የሚታቀብ ከሆነ መንግስት ለህዝቡ ማንኛውንም ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያደርስ አረጋግጠንላቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

አሸባሪው ህወሐት በመንግስት የተሰጡትን የሰላም አማራጮች እና የመንግስትን የተናጠል ተኩስ አቁም ባለመቀበል በጥፋቱ መቀጠሉን ሃላፊዋ እንድረዱ ተደርጓል።

ቡድኑ በከፈተው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው ለከፍተኛ ችግርና እንግልት መዳረጋቸውንም አስረድተናቸዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ለተፈጠሩት ወቅታዊ ችግሮች ከጅምሩ እስካሁን የህወሃት የሽብር ቡድን ጥፋት መሆኑን ማስረዳት መቻሉን የሰላም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።