መንግስት በጦርነት የተጎዱ አከባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት የሲቪል ማህበራት ማገዝ አለባቸው ተባለ

ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

ኅዳር 9/2015 (ዋልታ) መንግስት በጦርነት የተጎዱ አከባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት የሲቪል ማህበራት በግንባር ቀደምትነት ማገዝ እንደሚኖርባቸው የፍትህ ሚኒስትር እና የፌዴራል መንግስት የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባል ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም በተፈረመው የሰላም ስምምነት ሂደት፣ ውጤት እና አንድምታ ዙሪያ ለሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነትን ባስከበረ መልኩ መጠናቀቁን የገለጹት ሚኒስትሩ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር እና በግዛት አንድነት ላይ ተደቅኖ የነበረውን አደጋ በመቀልበስ ግጭቱን በዘላቂነት በማቆም ዜጎች እፎይታ እንዲያገኙ የማድረግ ግብ እንደነበርም ገልጸዋል።

በግጭቱ በዜጎች ላይ የደረሰውን የህይወት፣ የአካል፣ የስነልቦና እንዲሁም ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአካባቢውን ማህበረሰብ መልሶ ለማቋቋም ምቹ ሁኔታ መፍጠርም የሰላም ንግግሩ ዋና ዓላማ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ከግጭቱ ጋር በተገናኘ በአገር ኢኮኖሚ እና በዲፕሎማሲ ላይ ተደቅኖ የነበረውን ፈተና ማስወገድ የኢትዮጵያ ፅኑ አቋም ነው ያሉት ሚኒስትሩ በሰላም ስምምነቱም ግቦች መሳካታቸውን አንስተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ እስካሁን በቆመችለት የሰላም ጥሪና በመርሆዎቿ ሙሉ መፅናቷንና የሰላም አማራጩ መሳካቱን ጠቁመዋል፡፡

መንግስት የሰላም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅሰው የሰብዓዊ ድጋፍ፣ የአገልግሎት ማስጀመር፣ የመልሶ ግንባታና መሰል ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

የሲቪል ማህበራት በሀገር ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረት በግንባር ቀደምትነት ማገዝ እንዳለባቸውም ነው ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት።

በተለይም በዜጎች ላይ የደረሰውን የስነ-ልቦና ጉዳት ለማከም እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ሂደቱ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በመጠቆም።

ለዚህም ሃብት በማሰባሰብ የትምህርት ተቋማትን፣ የጤና ተቋማትን እንዲሁም ሌሎች የህዝብ መገልገያ ተቋማትን መልሶ በመገንባት ሀገራዊ ሚናቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ ተተግብሮ ህዝቡ በዘላቂነት እፎይታ እንዲያገኝ የሲቪል ማህበራት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

ሄኖክ መለሰ

ለዚህም መንግስት የሚያደርገውን የመልሶ ግንባታ ስራን መደገፍን ጨምሮ በሁሉም መስክ በትኩረት እንዲሰሩ ነው የጠቆሙት፡፡

በማብራሪያው ላይ የተገኙ ሲቪል ማህበራት አመራሮችና ተወካዮች በሰጡት አስተያየት የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያ በተግባር ማሸነፏን ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ሁሉም ወገን ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት ጠቁመው የሲቪል ማህበራት የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠው የሰላም ስምምነቱ በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት መሆኑንን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።