መንግስት ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ

ጳጉሜ 5/2013 (ዋልታ) መንግስት አሸባሪውና ወራሪው ቡድን በከፈተው ጦርነት ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ መልሶ ለማቋቋም ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ።

ሚኒስትሯን ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ የተጠለሉ ወገኖችን እየጎበኙ ነው።

በጉብኝቱ ወቅት ሚኒሰትሯ እንደገለጹት፣ በወቅታዊው ችግር የተፈናቀሉ ወገኖችን መደገፍና መንከባከብ ከሁሉም ይጠበቃል።

የደሴ ከተማና የአካባቢው ህዝብ ተፈናቃዮችን ተቀብሎ የሚያደርገው እገዛና ድጋፍ የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ ተናግረዋል።

መንግስት የተፈናቃዮችን ትክክለኛ መረጃ አጣርቶ ከሚያደርገው ሰብዓዊ ድጋፍ ባለፈ መልሶ ለማቋቋም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

“ተፈናቃዮች ለከፋ ማህበራዊ ቀውስ እንዳይጋለጡ በአጭር ጊዜ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በቅንጅት እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ከፌደራል የተውጣጣ ልዑክ ዛሬ ተፈናቃዮችን የጎበኘበት ምክንያት ያሉበትን ሁኔታ በአካል ለማየትና ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡና ተቋማት የጀመሩትን ሰብዓዊ ድጋፍና አጋርነት አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም ሚኒስትሯ አስገንዘበዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ በጉብኝቱ የፌደራል፣ ክልልና ዞን አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።