መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሐምሌ 26/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል አስፈላጊው የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ረገድ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በጂቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በጅቡቲ አዲስ ከተሾሙት የአልጄሪያ አምባሳደር ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ ጋር ላላት ግንኙነት ከፍተኛ ትኩረት እንደምትሰጥ አምባሳደር ብርሃኑ በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት አልጄሪያ በ1962 ነፃ ከመውጣቷ በፊት ፀረ ቅኝ ግዛት ትግል በጋራ ማድረጋቸውን አንስተው ሀገራቱ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ስትራቴጂካዊ ትብብር እንዳላቸውም አስረድተዋል።

አምባሳደሩ አክለውም ለአልጄሪያ አቻቸው የኢትዮጵያ መንግስት ሁሉም አስፈላጊ ሰብአዊ ድጋፎች ትግራይ ክልል መድረሳቸውን በማረጋገጥ ላይ ስላደረገው የማያወላውል ቁርጠኝነት አብራርተዋል።

አምባሳደሮቹ በሌሎች ቀጠናዊና አህጉራዊና አለማቀፋዊ ጉዳዮችም ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።