መንግስት የሠራተኛ አስተዳደር ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት መሰረታዊ መሆኑን ይገነዘባል

የካቲት 29/2015(ዋልታ) የኢትዮጵያ መንግስት የሠራተኛ አስተዳደር ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት መሰረታዊ መሆኑን እንደሚገነዘብ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

49ኛ የአፍሪካ ቀጠናዊ የሠራተኛ አስተዳደር ማዕከል (Africa Regional Labour Administration Center -ARLAC) ጉባኤ የአባል ሀገራቱ ሚኒስትሮች በተገኙበት በይፋ ተክፍቷል ፡፡

በመክፈቻው ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አሰግድ ጌታቸው የኢትዮጵያ መንግስት የሠራተኛ አስተዳደር ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት መሰረታዊ መሆኑን ይገነዘባል ብለዋል፡፡

የሚኒስትር ዴኤታው ዕለቱን አስመልክተው የአፍሪካ ቀጠናዊ የሠራተኛ አስተዳደር ማዕከል አፍሪካውያን የጋራ የሆኑ የሠራተኛ አሰተዳደር ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የማዕከሉ አባል ሀገር እንደመሆኗ ተጠቃሚ ሆናለች ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ መንግስት የልማት ግቦቹን ለማሳካት ማህበራዊ ጥበቃ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ያምናል ብለዋል::

መንግሥት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በእርጅና፣ በአካል ጉዳት፣ በፆታ ፣ በአደጋ እና መሰል ችግሮች በህግ የተደነገጉ ጥበቃዎችን እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

የሰራተኛ አስተዳደር ውስጥ ዋና ዋና ባለድርሻ አካላትን አሰባስቦ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው የአሰሪና ሥራተኛ አስተዳደርን በተመለከተ የሚስተዋሉ የስደተኛ ሠራተኞች ጉዳይ እና መደበኛ ያልሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደ አህጉር የወቅቱ ፈተናዎች በመሆናቸው ተባብረን ልንሰራባቸው ይገባልም ብለዋል፡፡

የአባል አገራቱ ሚኒስትሮች በዚህ ስብሰባ ዋና አጀንዳቸው በዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) በማህበራዊ ጥበቃ ስትራቴጂካዊ ዓላማ ላይ ለመወያየት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማህበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ለሠራተኞች ኑሮ መሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ ጠንካራ የሥራ አስተዳደር እንዲኖር የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለመስራት እንደሚጠቅምም ገልጸዋል፡፡

19 አባል ሀገራቱ እና ታዛቢ ሀገራትም ጭምር በኮቪድ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰራተኞቻቸውን የሚደጉሙባቸውን ሁኔታዎች በተመለከተም ውይይት መደረጉን እና በባለሙያዎች የተዘጋጀው ሰነድ እንደሚፀድቅ መናገራቸን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ፡፡