መከላከያ ሚኒስቴር አዲስ የተሸከርካሪ ሰሌዳ በማዘጋጀት በአገልግሎት ላይ አዋለ

ነሐሴ 27/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር አዲስ የተሸከርካሪ ሰሌዳ በማዘጋጀት በአገልግሎት ላይ ማዋሉን አስታወቀ፡፡

የመከላከያ ሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ የሠራዊቱን አሁናዊ ዝግጁነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጾ ለተዋጊ ክፍሉ ግዳጅ አፈፃፀም ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ የተለያዩ ሞዴል ያላቸውን ቀላል ተሸከርካሪዎች ስታንዳርድ በማዘጋጀት ለዕዞችና ለክፍሎች የቁልፍ ርክክብ ማድረጉን አመልክቷል፡፡

የተሸከርካሪዎችን ቁልፍ ለሁሉም ዕዞች እና ለተለያዩ ተዋጊ ክፍል አመራሮች ያስረከቡት የመከላከያ ሎጅስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀኔራል አብዱራህማን እስማኤል ተቋማቸው መከላከያ የሠራዊቱን ዝግጁነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉና ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ ተሸከርካሪዎችን ማደል መቻሉን ገልጸዋል።

በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና ሙያተኞች ለንብረቱ ደህንነት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እየታየ ያለውን የንብረት አያያዝ ክፍተት በመቀነስ ጥንቃቄ በማድረግ ስምሪት በመስጠትና በመቆጣጠር ማስተዳደር እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

ተቋሙ ከዚህ ቀደም ሲጠቀምበት የነበረውን የተሸከርካሪ ሰሌዳ በአዲስ ሠሌዳ የቀየረ መሆኑን እና ከነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተሸከርካሪዎች ላይ በመለጠፍ አገልግሎት መጀመሩን ያበሠሩት ኃላፊው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሁሉም የተቋሙ ተሸከርካሪዎች አዲስ ሰሌዳ እንደሚደርስም ገልጸዋል።

በተለያየ ምክንያት የተቋሙ በርካታ ሠሌዳዎች ከተቋሙ እውቅና ወጪ በሌሎች እጅ መገኘቱ ለህገ-ወጥ ተግባር እንዳይውሉ ለመከላከል ታሳቢ ተደርጎ ሠሌዳው የተቀየረ ሲሆን አሁናዊ የሠራዊቱን ተልዕኮ እና ግዳጅ መነሻ አድርጎ በሚሰጡት አገልግሎት መሰረት በኮድ ጭምር ተለይተው የተዘጋጁ ናቸውም ብለዋል።

የተቋማችንን የንብረት አስተዳደር ቁጥጥር ሂደት ውጤታማ ለማድረግ የሚያሥችል በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ለዚህ ዓላማ መሳካት አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር፣ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ በተጠያቂነት መንፈስ ማስተዳደር እንዳለባቸው መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡

በእለቱ በቦታው የተገኙት የሁሉም ክፍል አመራሮች በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት ለተግባራዊነቱ ዝግጁ መሆናቸውን በማረጋገጥ ቁልፍ መረከባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡