መከላከያ ሰራዊቱ በከፈለው መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ከብተና ያዳነ ሀይል ነው- አቶ አገኘሁ ተሻገር

አገኘሁ ተሻገር

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በከፈለው መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ከብተና ያዳነ ሀይል ነው ሲሉ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

ሰራዊቱ በህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው የፈፀመው ግዳጅ ህዝቡ ለሰራዊቱ የነበረውን የተዛባ አተያይ ያከመበት ነው ብለዋል።

ከሃዲው የጁንታ ቡድን ስብስቦች በአገሪቱ በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ ሀይሎች ጣምራ ክንድ ፈጥረው ለጋራ ሰላማችን እንዳይተጉ መዋቅራዊ አደረጃጀት በመዘርጋት የአፍራሽነት ሚና ሲወጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

የህወሓት ሀይሎች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይከሰቱ የነበሩ ዘርና ብሄር-ተኮር ግጭቶችን ከመወጠን ጀምሮ የእኩይ አላማቸው ፈፃሚ የሆኑ ሀይሎችን በመመልመል፣ በማሰልጠንና በማሰማራት የህዝቦችን አብሮነታዊ ሰላምና ማንነታዊ አንድነት ሲያደፈርሱ ኖረዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በህልውና ዘመቻው መላው የአማራ ክልል ህዝብ፣ ባለሀብቶች፣ የህክምና ባለሙያዎች እና በየከተሞቹ የሚገኙ እናቶች የላቀ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ብለዋል።

ልክ እንደ ከሃዲ ጁንታዎች ሁሉ አሁን ላይ የሌላ ሀይል ጉዳይ አስፈፃሚ የሆኑትን የሱዳን ተንኳሽ ሀይሎችን ጨምሮ እየታዩ ካሉ አገራዊና ከባቢያዊ አዝማሚያዎች አንፃር እንደ አገር ህብረታችንን አጠንክረን ከሰራዊታችን ጎን የምንቆምበትን በር የሚከፍትልን ነው ሲሉም አክለዋል።

የአማራ ክልል ህዝብና መንግስት በየትኛውም መልኩ በሚያስፈልጉ ድጋፎች ሁሉ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጎን እንደሚቆሙ አቶ አገኘሁ ተሻገር ማረጋገጣቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡