ጥቅምት 13/2014 (ዋልታ) የአገር መከላከያ ሰራዊት በአሸባሪው ሕወሓት ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።
ለንፁሃን ደኅንነት ጥንቃቄ ያደረገው የአገር መከላከያ ሰራዊት ትላንት በ4ኛ ቀን የአየር ድብደባው የአሸባሪውን ሕወሓት የወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከልን ዒላማ እንዳደረገ መንግሥት ማሳወቁ ይታወሳል።
ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ግን በአገር መከላከያ ሰራዊት የአየር ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ በረራ ተሰናክሏል ሲል ዘግቧል ።
በዚህም የአየር ጥቃት ወደ ትግራይ ክልል የሚጓዘው የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ እርዳታ የአየር በረራዎች ተቋርጠዋል ሲሉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድርጅት ቃል አቀባይ ስቲቭ ታራቬላ ተናግረዋል ሲል ጽፏል።
ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ወደ ትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ የሚያደርጋቸውን በረራዎች በሙሉ ማገዱን ያሳወቁት የመንግሥታቱ ቃል አቀባዩ ስቴፋን ዱጃሪክ ከፌደራል መንግሥት የበረራ ፈቃድ ተገኝቶ ቢበርም በመቀሌ ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያ የበረራ ተቆጣጣሪዎች እንዳያርፍ ትዕዛዝ ሰጥተው እንደመለሱት ትናንት ማሳወቃቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት ለወራት በትግራይ ክልል የሰብኣዊ እርዳታ ለማድረስ እንቅፋት እንደነበረባቸው ቅሬታ ሲያሰሙ ነበር ሲልም ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ያስነበበው። እንቅፋቱን እየፈጠረ ያለው ግን ጦርነቱን ወደ አጎራባች ክልሎች እያስፋፋ ያለው አሸባሪው ሕወሓት ስለመሆኑ ዘገባው መጥቀስ አልፈለገም።
ይህንን ተከትሎም የትግራይ ተወላጇ የሲቢኤስ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ዘ ኒውዮርክ ታይምስ የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ እረዳታ በረራ በአየር ጥቃቱ ተሰናክሏል ሲል ላወጣው ዘገባ እርምት ሰጥታልች።
ለብዙ ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት በመቶዎች ለሚቆጠሩ የተባበሩት መንግሥታት እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ፈቅዷል ብላለች፤ ሄርሜላ በቲውተር ገጿ የዘ ኒውዮርክ ታይምስ ሚዛን የሳተ ዘገባ ሊታረም እንደሚገባው በጠቀሰችበት መልዕክቷ።
ጋዜጠኛ ሄርሜላ የመንግሥታቱ ባለሥልጣናት ተሽከርካሪዎችን እና ሌሎች መሳሪያዎችን በሺሕዎች የሚቆጠሩ ንጹሃ ዜጎችን በግፍ እየገደለ ላለው ሕወሓት የሽብር ቡድን ሰጥተዋል ነው ያለችው።
የዘ ኒው ዮርክታይም ዘገባም የጋዜጠኝነት ስነምግባር የጎደለው ነው ያለች ሲሆን በውጭ አገራት ላይ ጦርነትን የሚያቀጣጥል ነዳጅ የመጨመር ፍላጎት እንደሆነ ነው የተቸችው።