መከላከያ ሰራዊት የሱዳን መንግሥት እንደሚለው በቦታው ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱን ገለጸ

ሰኔ 21/2014 (ዋልታ) የሱዳን መንግሥት እንደሚለው የመከላከያ ሰራዊት በቦታው ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱንና ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት እንዳልፈፀመ የመከላከያ ሰራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሰሞኑ የሱዳን መንግሥት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት የማረካቸውን ወታደሮቼን ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት ፈፅሟል ብሎ ባወጣው መግለጫ ዙሪያ ምላሽ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያና ሱዳን የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራትና በሕዝቦች መካከል የረጅም ታሪክ የአብሮነት መስተጋብር ያላቸውና በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻቸውን ሲፈቱ የነበሩ ሀገራት እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ይሁንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት በሀገርና በሕዝብ ላይ ክህደት ከፈፀመ ወዲህ ሱዳን የውስጥ ችግሮችን እንደ እድል በመጠቀም የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ መግባቷን የመከላከያ ሰራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ተናግረዋል።

ይህንንም ድርጊት የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እስካሁን መታገሱንም ጠቁመዋል፡፡

የሱዳን ሰራዊት ወረራ በፈፀመበት ቦታ ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር የተፈጠረ ግጭት መኖሩንና በሁለቱም በኩል ተጎጂዎች መኖራቸውን ያነሱት ኮሎኔል ጌትነት ሆኖም የሱዳን መንግሥት እንደሚለው የመከላከያ ሰራዊት በቦታው ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱንና ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት እንዳልፈፀመ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሥነ ምግባር የታነፀ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው ለዚህም ማሳያ የቀደመው የኮንጎና የኮርያን ሰላም ማስከበር በተለይም ደግሞ የቅርቡን በሁለቱ ሱዳኖች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሁለቱ ሀገራት ተመርጦ ሰላም ለማስከበር አብየ ግዛት በመግባት ግዳጁን የተወጣ ጨዋ መሆኑን አብራርቷል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሕግና በሥርዓት የሚመራ መሆኑን አውስተው የሱዳን መንግሥት በወረራ ከያዘው የኢትዮጵያ መሬት እንዲወጣ መንግሥት የሰላም አማራጮችን ክፍት በማድረጉ መከላከያ የወሰደው አጸፋዊ እርምጃ አለመውሰዱንም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የሰላም አማራጮችን ክፍት ማድረጉንና አሁን ተፈጠረ የተባለው ግጭት በገለልተኛ አካልም ሆነ የሁለቱ መከላከያ አመራሮች በተገኙበት እንዲጣራ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሳራ ስዩም