መደመር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ብሔራዊ አንድነት በሚል የፓናል ውይይት ነገ በአሶሳ ይካሔዳል

መስከረም 23/2016(አዲስ ዋልታ)  መደመር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የፓናል ውይይት በነገው እለት በአሶሳ ከተማ ይካሄዳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገር በቀል እውቀቶችን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ የምትመራበትን የመደመር እሳቤ ተግባራዊ ያደረጉ ሲሆን፤ እሳቤው ለትውልድ እንዲተላለፍም “መደመር” ፣ “የመደመር መንገድ” እና “የመደመር ትውልድ “ የሚሉ መጽሃፍትን ለንባብ አብቅተዋል።

ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመጽሃፍቱ የሰፈሩ ሃሳቦች ላይ ውይይት በማድረግ በእሳቤው ለተቀመጡ ግቦች መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስገንዘባቸው ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም ኢዜአ “የመደመር ጉዞ” በሚል ማዕቀፍ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፉ የፓናል ውይይት መድረኮችን በተለያዩ ከተሞች እያካሄደ ይገኛል።

የመድረኮቹ ዋነኛ ዓላማም በመደመር እሳቤ ላይ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር ሀገራዊ አንድነትና አብሮነትን ማጠናከር ነው።

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ እና ጅግጅጋ መሰል የውይይት መድረኮች የተካሄዱ ሲሆን፤ በነገው እለት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የሚያካሂደው መድረክም ምዕራፍ አራት መሆኑ ተገልጿል።

የምዕራፍ ሶስት መድረክ “መደመር የዘመኑ አርበኝነት” በሚል መሪ ሃሳብ ባሳለፍነው ነሃሴ ወር በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

በመድረኩም የመደመር እሳቤ ላይ ትኩረት ያደረጉ አራት የውይይት መነሻ ሃሳቦች ቀርበው ሰፊ ምክክር ተደርጎባቸዋል።

በወቅቱ የመደመር እሳቤ አገርን በተሰናሰነ አቅም ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል የዘመኑ አርበኝነት መሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ ሃሳቦች መነሳታቸውም ይታወሳል።

በነገው እለት የሚካሄደው መድረክም የመደመር እሳቤ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታና ብሔራዊ አንድነት ያለው ሚና ላይ ትኩረት ያደረጉ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።

በውይይት መድረኩም የክልሉና የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም በክልሉ የሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እንደሚሳተፉ ታውቋል።