መድኃኒቶችን ተሸክሞ ረጅም ርቀት በእግሩ በመጓዝ የበርካቶችን ህይወት የታደገው ሃኪም

መድኃኒቶችን ተሸክሞ ረጅም ርቀት በእግሩ በመጓዝ የበርካቶችን ህይወት የታደገው ሃኪም

“በቦረና በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ሄደን ጎርፍ አስቸግሮናል” – ዶክተር በላይነህ ለታ

በሳሙኤል ሙሉጌታ

 

ዶክተር በላይነህ ለታ ይባላሉ፤ የህፃናት ስፔሻሊስት ሀኪምና የኦሮሚያ ሃኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡  ህክምና በጤና ተቋማት ብቻ መወሰን የለበትም የሚሉት ሃኪሙ የጤና አገልግሎትን ላቅ ወዳለ ደረጃ እያደረሱት የሚገኙ ምስጉን ባለሙያ ናቸው፡፡

ህክምና ሌሎችን ለማገልገል የተሰጠ ሙያ ወይም በረከት ነው የሚሉት ዶክተሩ እርዳታ በሚያስፈልግበት አካባቢዎች ሁሉ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒታቸውን አንግበው በእግር በመኪና መንገዶችን ለማቆራረጥ የሚቀድማቸው የለም፡፡

ከዚህ በፊት በወለጋ፣ በጉጂ፣ በሶማሊያ፣ በምዕራብ አርሲ፣ በባሌ ዞን እና ሌሎች በርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ሀይማኖትም ሆነ ብሔር ሳይለዩ የብዙዎችን ጤና አክመዋል፡፡ እንባ አብሰዋል፡፡ ሳቅ መልሰዋል፡፡

ዶክተር በላይነህ እና የሙያ ባልደረቦቻቸው እንደወትሮው ሁሉ ከሰሞኑ በበርካታ መገናኛ ብዙኃን በኩል መነጋገሪያ የነበረውን የቦረና ድርቅ ተከትሎ የተጎዱ ማህበረሰቦችን ለማገዝ ወደ አካባቢው አምርተው ነበር፡፡

ዶክተር በላይነህ ወደ አካባቢው ያመሩት ግን ለብቻቸው አይደለም፡፡ በሦስት ስፔሻሊስቶች እና ዘጠኝ ጠቅላላ ሃኪሞች የተዋቀረ ቡድንን ይዘው ሲሆን ከተለያዩ አካላት የህክምና መድኃኒት በማሰባሰብ ወደ ቦረና ጉዞ ለማድረግ ሲነሱ ሁለት አላማዎችን አንግቦ ነበር፡፡

የመጀመሪያው በድርቁ የተጎዱ ማበረሰቦችን በየጉራንጉሩ ሳይቀር እየገቡ ህክምና መስጠት ሲሆን በመቀጠልም በአካባቢው የሚስተዋሉ አሳሳቢ ችግሮችን በመለየት ለሚመለከተው አካል በተለያየ መንገድ ለማሳወቅ ነው፡፡

በአካባቢው ላይ ከደረሱ በኃላ በተለያየ መንገድ ህብረተሰቡን ያገለገሉ ሲሆን በምጥ ላይ የነበሩ እናቶችን አገላግለዋል፤ የወለዱ እናቶች ከወሊድ በኃላ የሚገጥማቸውን እክል ቀርፈዋል፤ መደበኛ መዳኃኒታቸውን ጨርሰው በነብስ ግቢ ነብስ ውጪ ላይ የነበሩ ለስኳር እና ደም ግፊት ህሙማን ከኪሳቸው ብር አውጥተው ጭምር መድኃኒት በመግዛት ህይወት ታድገዋል፡፡

እነ ዶክተር በላይነህ የበጎ አድራጎት ስራቸውን እያከናወኑ እያሉ አንድ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ ከየት መጣ ያልተባለ ከባድ ዝናብ በአከባቢው ላይ የጣለ ሲሆን ተሽከርካሪ በመጠቀም በአካባቢው ላይ አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች ሆነ፤ በዚህ ጊዜ እነ ዶክተር በላይነህ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ መኪናቸውን ባለበት አቁመው የህክምና መድኃኒቶችን ተሸክመው ለእንግዳ ሰው የማይደፈረውን ጫካ ከጎርፍ ጋር እየታገሉ ለማቋረጥ ወሰኑ፡፡

ረጅም ርቀት መጓዝ ብቻ ሳይሆን የህክምና መድኃኒትን ተሸክሞ መጓዝ ሌላ ፈተና ነው የሚሉት ዶክተር በላይነህ ፈተናው የአካባቢው መልከዓ ምድርን መጋፈጥንም ይጨምራል ይላሉ፡፡

ነገር ግን ዶክተሩ እንዲህ ይላሉ…. እኛ የተጋፈጥነው ፈተና ከህዝባችን ችግር አንፃር ኢምንት በመሆኑ ከረጅም ጉዞ በኃላ በርካታ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ህይወት መታደጋችን ከምንም በላይ ለእኛ ልዩ የመንፈስ እርካታ ነው የሰጠን ይላሉ፡፡

የህክምና አገልግሎታቸው በአንድ ቦታ የተወሰነ ብቻ ያልነበር ሲሆን ከቤት ለቤት አገልግሎት አንስቶ እስከ መጠሊያ በመዘዋወር በቀን እስከ 340 ለሚሆኑ ነዋሪዎች ህክምና እየሰጡ ሁሉ እንደነበር ዶክተር በላይነህ ለታ ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውሰዋል፡፡

ይህንን የቤት ለቤት የህክምና አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅትም የገጠማቸውን አሳዛኝ ታሪክ አጫውተውናል፡፡ አንዲት እናት በቀላሉ ሊታከም የሚችል ነገር ግን የህክምና አገልግሎት ባለማግኘታቸው ብቻ የዓይን ብርሃናቸውን እንዳጡ በተሰበረ ልቦና ገልጸውልናል፡፡

በቦረና ዞን አሁን እየተደረገ ስላለው ድጋፍ ሲገልጹ በከተማ አካባቢ የሚገኙ ተጎጂዎች በቂም ባይሆን የእለት ደራሽ ድጋፍ እና የህክምና አገልግሎት እያገኙ ነው ሲሉ ራቅ ባሉ የገጠር አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የድርቁ ተጋላጮች ግን አሁንም በቂ ድጋፍ እያገኙ ባለመሆናቸው ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡

ዝናብ ዘነበ ማለት የአካባቢው ችግር ተፈታ ማለት አይደለም የሚሉት ዶክተር በላይነህ በርካታ ዜጎች የመጠለያ ችግር ስላለባቸው ዝናቡን ተከትሎ ችግራቸው ይባባሳል እና ተገቢው ትኩረት ሊሰጠቸው ይገባል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡