መገናኛ ብዙሃን እየጨመረ የመጣውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚመጥን የሳይበር ደህንነት እውቀት ሊኖራቸው ይገባል – ዶክተር ሹመቴ ይግዛው

ዶክተር ሹመቴ ይግዛው

ግንቦት 25/2013 (ዋልታ) – መገናኛ ብዙሃን እየጨመረ የመጣውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚመጥን የሳይበር ደህንነት እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ይግዛው ገለጹ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በመተባበር ለሚድያ ባለቤቶችና ባለሙያዎች የሳይበር ደህንነትን አስመልክቶ የአንድ ቀን ኮንፈረንስ አዘጋጅቷል።

በመድረኩ መገናኛ ብዙሃን እየጨመረ የመጣውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን የሚመጥን የሳይበር ደህንነት እውቀት አለመኖራቸው ተገልጿል፡፡

የኮንፈረንሱ መጀመርን አስመልክተው የኢንፎርሚሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ይግዛው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሚድያዎች ቴክኖሎጂን የመጠቀምና መረጃን በጥራትና በፍጥነት የማድረስ አቅም እያደገ ቢመጣም ይህን የሚመጥን የሳይበር ደህንነት ክህሎት አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ ሀገራዊ ሪፎርሞች ማድረጓን ተከትሎ በርካታ የሳይበር ጥቃት መሰንዘራቸውን አስታውሰው፣ በመጪው ወራት የሚደረገው ሀገራዊ ምርጫና ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌትን ተከትሎ ሊሰነዘሩ የሚችሉ የሳይበር ጥቃትን ለመመከት ለሚድያ ባለሙያዎች ግንዛቤ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣ ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፣ ሚድያዎች የሚያሰራጩት መረጃ ተአማኒነቱን ከመጠበቅ ባለፈ ለሳይበር ደህንነት ትኩረት እና እውቀት መኖር አስገዳጅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመድረኩ በወቅታዊ ጉዳዮች የሳይበር ደህንነትና የመገናኛ ብዙሃን ሚና በሚል የተዘጋጀ ሰነድ ለተሳታፊዎች እየቀረበ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።