መገናኛ ብዙኃንና የማኅበረሰብ አንቂዎች ሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ ሊሠሩ ይገባል

ግንቦት 27/2014 (ዋልታ) መገናኛ ብዙኃንና የማኅበረሰብ አንቂዎች ተደማጭነታቸው ሰፊ ስለሆነ በትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ አተኩረው ሊሠሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመለከተ።

የጉባኤው ዋና ጸሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በልጆች ምግባር ላይ ለውጥ ለማምጣት ከመምህራን፣ ከትምህርት ማኅበረሰቡና ከሃይማኖት አባቶች ጋር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

የሃይማኖት አባቶች በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በማቅናት ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዲበረቱና በሥነ ምግባራቸው እንዲጎለብቱ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በትምህርት ቤት እንደማሳለፋቸው መጠን ሰፊ የሥነ ምግባር ቀረጻ ሥራ እንደሚስፈልግ የተናገሩት ዋና ጸሐፊው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትምህርት ቤቶች ዙርያ የሚታዩ ሁኔታዎችን ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል።

በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ሀገር በቀልና ሃይማኖታዊ እሴቶቸ እንዲካተቱ ለማድረግም ጉባኤው እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ነው መጋቢ ታምራት የተናገሩት።

ወላጆች ልጆቻቸውን በግብረገብነት አንጸው እንዲያሳድጉ ለማድረግ ጉባኤው ለሃይማኖት መምህራን ስልጠና በመስጠት ጉዳዩን በአስተምህሯቸው እንዲያካትቱ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በሌላ በኩል መገናኛ ብዙኃን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች ተደማጭነታቸው ሰፊ ስለሆነ በትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።