“መጨረሻ የምናደርገውን ውይይት ጥፋት ከመድረሱ በፊት አስቀድመን እናድርግ ብለን ብዙ ጥረቶች አድርገናል” – ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

ግንቦት 21/2016 (አዲስ ዋልታ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸው የአማራ ክልል ከ2015 ዓ.ም ሐምሌ መጨረሻ ጀምሮ የሰላም ችግር እንደገጠመው አስታውሰዋል። የክልሉ ሕዝብ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደነበርም ተናግረዋል። የሰላሙ ችግር የክልሉን የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እና በሌሎች ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ገልጸዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ሊሠሩ የታቀዱ ሥራዎች መስተጓጎላቸውንም አመላክተዋል። በመጀመሪያ ችግሩን ለመቀልበስ የሚያስችል ስልት ነድፈው መንቀሳቀሳቸውን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ የፖለቲካ እና የመንግሥት አሥተዳደርን እንደገና የመገንባት ሥራ አቅደን ሠርተናል ነው ያሉት።

እንደገና የተደራጀውን አሥተዳደር የማጽናት ሥራ መሠራቱንም አስታውቀዋል። የታጠቀው ኃይል ያለመው ዓላማ እንዳይሳካ የማድረግ፣ የመንግሥት እና የፖለቲካ አደረጃጀቶችን እንደገና የመገንባት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። የታጠቀው ኃይል እንቅስቃሴው በተወሰኑ ቆላማ እና ኪስ ቦታዎች ላይ እንዲገደብ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል። እንዲህ አይነት ድርጊት እንደማይሳካ ትምህርት እንዲወስድ አድርገናልም ነው ያሉት።

የታጠቀውን ኃይል እቅድ ማክሸፋቸውን እና መንግሥት ደግሞ ወደ መደበኛ የልማት ሥራዎች መመለሱንም ገልጸዋል። የክልሉ የጸጥታ ችግር እንዲሻሻል ላደረገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይል፣ የክልሉ መሪዎች እና ለክልሉ ሕዝብ ምሥጋና ይገባል ብለዋል። የሕዝቡ አስተዋይነት እና አረዳድ የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል። መንግሥት እና ፓርቲው ባሉ ጉድለቶች ላይ ትምህርት መውሰዳቸውንም ገልጸዋል።

የክልሉ ሕዝብ እንዲህ አይነት ችግሮችን እንዴት መከላከል እንዳለበት ትምህርት ወስዷል ነው ያሉት። በችግሩ ውስጥ ለአማራ ክልል ተስፋ ሰጪ እድሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በጥንቃቄ ማየት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ግጭቶች ችግሮች እንዳይደገሙ ትምህርት የሚወሰድባቸው እና ወደ ላቀ ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችሉ እድሎችን ሊፈጥሩ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

“የአማራ ሕዝብ ያደሩ እና አሁን ድረስ እንዲፈቱለት የሚፈልጋቸው ጥያቄዎች አሉት” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የማንነት እና የራስ አሥተዳደር፣ የተዛባ ትርክት እንዲታረም፣ የኢኮኖሚ ኢ-ፍትሐዊነት፣ ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል እና ሌሎች ጥያቄዎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። ጥያቄዎቹ ለረጅም ጊዜ የቆዩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። ጥያቄዎችን ለመፍታት የፌዴራል መንግሥት፣ የክልሉ መንግሥት እና ብልጽግና ፓርቲ አጀንዳ አድርገው እየሠሩ ነው ብለዋል።

የማንነት ጥያቄ ባለባቸው አካባቢዎች ጥያቄው እንዴት መፈታት እንዳለበት ግልጽ አቅጣጫ መኖሩንም ገልጸዋል። ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራበት መኾኑንም አመላክተዋል።

ሕገ መንግሥቱም በሚገባው መንገድ መሻሻል አለበት የሚል አቋም መኖሩንም ገልጸዋል። ጥያቄዎች በስምምነት እና በውይይት የሚፈቱ እንጂ በጦርነት የሚፈቱ አለመኾናቸውንም አመላክተዋል። መንግሥት ጥያቄዎችን ለመፍታት በውይይት እና በድርድር እንደሚያምንም ገልጸዋል።

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ ሰዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተሰደዋል ነው ያሉት። መኾን በሌለበት፣ ትርጉም በሌለው፣ የአማራን ሕዝብ በማይጠቅም ጉዳይ ሰብዓዊ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

በክልሉ የግለሰብ፣ የማኅበረሰብ እና የመንግሥት ተቋማት መውደማቸውንም ገልጸዋል። በግጭቱ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ከሕዝብ በተሰበሰበ ግብርና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተገነቡ የአሥተዳደር ተቋማት እንዳልኾነ ኾነዋል ነው ያሉት።

የኢንቨስትመንት ቦታዎች ውድመት ደርሶባቸዋልም ብለዋል። ግጭቱ የልማት ጥያቄ ላለው እና መልማት ለሚፈልግ ሕዝብ አንጡራ ሀብቱን ማውደሙንም አመላክተዋል። በግጭቱ ምክንያት ማኅበራዊ ትስስሮች መናጋታቸውንም ተናግረዋል።

የአማራ ሕዝብ ለአንድነቱ እና ለአብሮነቱ መሠረት የኾኑ የትስስር ገመዶች ተጎድተዋል ነው ያሉት። ሕዝቡ በልማት ተወዳዳሪ እንዳይኾን፣ ራሱን እንዳይጠቅም የሚያደርግ ትልቅ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል።

ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች መደረጋቸውን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት የተደረገው ግጭቱ ጉዳቶችን እንደሚያመጣ ስለምናውቅ፣ የአማራ ክልልን ሕዝብ እንደሚጎዳ ስለ ተገነዘብን ነው ብለዋል። የአማራ ሕዝብ ችግሮች በጦርነት እንደማይፈቱ ስለምንገነዘብ እና መጨረሻውም ቢሆን ውይይት እና ድርድር እንደሚኾን ስለምናውቅ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት አድርገናል ነው ያሉት። “መጨረሻ የምናደርገውን ውይይት ጥፋት ከመድረሱ በፊት አስቀድመን እናድርግ ብለን ብዙ ጥረቶች አድርገናል” ብለዋል።

ግጭቱ ከመፈጠሩ አስቀድሞ በተለያዩ ምክንያቶች ታጥቀው በጫካ ለሚገኙ ኃይሎች ጥሪ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ጥሪውን ተቀብለው የመጡ አካላትንም በእንክብካቤ ለመያዝ ጥረት አድርገናል ነው ያሉት። ወደ ጫካ እንዲገቡ ያደረጓቸውን ምክንያቶች ማወቅ፣ መጋራት፣ ከዚያም ተነስቶ በሀገር ግንባታ ላይ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ መንገር፣ ለዚያም ተሳታፊ እንዲኾኑ የሚያስችል ሥራ ሠርተናል ብለዋል።

የግል ሕይወታቸው እንዲስተካከል በተቻለ አቅም መሠራቱንም አስታውሰዋል። ከጫካ የመጡ በመኾናቸው በሌሎች አካላት ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥበቃም አድርገናል ነው ያሉት። ሰላማዊ ሕይወትን እንዲለማመዱ፣ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች እንዲመከሩ ጥረት መደረጉንም አስታውሰዋል።

ግጭቱ ከተፈጠረ በኋላም ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። ችግሮችን ለመፍታት አንደኛውም፣ ሁለተኛውም፣ ሦስተኛውም የሠላም አማራጭ ነው ብለን የሰላም ጥሪ አቅርበናል፤ ራሳችን በቀጥታ ጠርተናል፤ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችም የሰላም ጥሪ እንዲያደርጉ አድርገናል ነው ያሉት። ወንጀሎችን ይቅር የሚል፣ የነፍስ ወከፍ ትጥቆችን የሚፈቅድ የሰላም ጥሪ መደረጉንም አስታውሰዋል። የተደረጉ የሰላም ጥሪዎች ውጤት ማምጣታቸውንም ገልጸዋል።

መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ለሕዝብ ማሳየቱን እና ሕዝብ የቀረበውን የሰላም አማራጭ ማድነቁን ተናግረዋል። የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በሰላም ጥሪው መመለሳቸውንም አንስተዋል። በክልሉ ያለውን ግጭት የሚያባብሱ ሚዲያዎች መኖራቸውን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ ግጭትን የሚያባብሱ ኃይሎች የተለያየ ፍላጎት ያላቸው መኾናቸውንም ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው፣ ግጭቱን እንደ ገቢ ምንጭ የሚጠቀሙ እና እንደ ኑሮ ዋስትና አድርገው የሚሠሩ ኃይሎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት። የአማራ ክልልን በማተራመስ ረብጣ ዶላር የሚሰበስቡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ሚዲያዎች መኖራቸውንም አንስተዋል። የአማራ ክልል በእያንዳንዱ ሞት ከፍተኛ ገንዘብ የሚገኝበት ኾኖላቸዋል ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡ በግጭት ገንዘብ የሚሰበስቡ ሚዲያዎችን ፍላጎት መረዳት እንደሚገባውም አሳስበዋል። የሚያስከትለውን ውጤት እና የሚያመጣውን መዘዝ፣ የግለሰቦችን ፍላጎት ከሕዝብ ፍላጎት ጋር አመዛዝኖ መረዳት አለበት ነው ያሉት። ሕዝቡ ግጭት የሚያባብሱ ሚዲያዎችን ፍላጎታቸውን ካልተረዳ የጥፋት መሣሪያ ይኾናል ብለዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ቀዳሚው አጀንዳችን ነው ብለዋል። በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር መሥራት አለብን ነው ያሉት። በተለያየ ቦታ ያለውን ቡድን በተቻለ መጠን ውይይት በማድረግ ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ማድረግ ያስፈልገናል ብለዋል። ሰላምን ለማረጋገጥ ከማኅበረሰቡ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች እንደሚያስፈልግም መግለፃቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

በክልሉ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል በትኩረት የሚሠራበት ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል። ከሥራ አጥነት እና ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ይሠራል ነው ያሉት። የሕዝባችን ጥያቄ እንዲፈታ በንጽሕና፣ በአገልጋይነት መንፈስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንክረን መሥራት አለብን ነው ያሉት።

ርእሰ መሥተዳድሩ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሕዝቡም ሰላም እና እድገትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል ድጋፍ እንዲያድርግም አሳስበዋል። ችግሮችን በግጭት ሊፈታ የሚፈልገውን ኃይል አደብ እንዲያስገዛ፣ ትክክለኛ መንገድ እንዳልኾነ እንዲነግር፣ ተደራጅቶ እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለይም የአማራ ተወላጆች በሐሰተኛ መረጃዎች ሳይደናገሩ የክልሉ ሕዝብ ወደ ሰላም እንዲመጣ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ።