ሚኒስቴሩ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

ጥቅምት 1/2015 (ዋልታ) የግብርና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) ለመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ አስረክበዋል።

ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 64 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሲሆን ከ15 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተው ደግሞ የአይነት ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮፌሰር ኢያሱ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ድጋፉ የተቋማቱ ሠራተኞችና አመራሮች ለሀገር ህልውና ህይወቱን እየሰጠ ከሚገኘው ሠራዊት ጎን መቆማቸውን ለማሳየት ነው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በቀጣይ በሁሉም መስክ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ በበኩላቸው የግብርና ሚኒስቴርና በስሩ ያሉ ተጠሪ ተቋማት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።