ሚኒስቴሩ ለተፈናቃዮች ያደረገው የምግብና አልባሳት ድጋፍ

ጳጉሜ 1/2013 (ዋልታ) የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ16 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ምግብና አልባሳት ድጋፍ አደርጓል።

የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ድጋፉን ለአፋር ክልል መንግስት ያስረከቡ ሲሆን፣ አሸባሪው ህወሃት የደቀነብንን የህልውና አደጋ ለመመከት ህዝቡ ሴት ወንድ ሳይል መስዋእትነት እየከፈለ ነው “የከሀዲው ቡድን ግብአተ-መሬቱ በቅርቡ ይፈጸማል” ብለዋል።

የአሸባሪው አባላት በየደረሱበት ሁሉ በሴቶችና ህጻናት ላይ የአስገድዶ መድፈርና ተያያዥ ኢ-ሰብአዊ ጥቃቶችን መፈጸሙን አመልክተዋል።

“ዜጎች ላይ የተፈጸመን ችግር ለመቅረፍ ሁላችንም ከመንግስትና ተጎጂዎች ጎን በመቆም ከእለት ደራሽ እርዳታ እስከ ዘለቄታው የማቋቋም ስራዎችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በጋራ እናከናውናለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ አሸባሪው በከፈተው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች 16 ሚሊዮን 735ሺህ ብር ግምት ያለው ምግብና አልባሳት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረው፣ ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ ስኳር፣ ሩዝ፣  ሌሎች የምግብ ግብዓቶች እና 18 ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝን አልባሳት እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

የአፋር ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አይሻ ያሲን ድጋፉን ሲረከቡ እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በክልሉ በከፈተው የእብሪት ጦርነት በተለይም በንጹሃን አርብቶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል።

መስሪያ ቤቱ ያደረገው ድጋፍ የተጎጅዎችን ችግር ለማቃለል ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፣ ድጋፉ ለሌሎችም አስተማሪ የሚሆን በጎ ተግባር እንደሆነ መናገራቸውን የአፋር ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል።