ሚኒስቴሩ ለታርጫ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከ25 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በእሺ ፕሮግራም በዳውሮ ዞን ለሚገኘው ታርጫ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከ25 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ለአይሲቲ መሠረተ ልማት የሚሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የተረከቡት የኮሌጁ ዲን ኤፍሬም አይሳ ድጋፉ በሃገር ደረጃ በተመረጡ 20 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የአይሲቲ መሠረተ ልማት የማስጀመር እቅድ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም የተደረገው ድጋፍ የኮሌጁን የቴክኖሎጂ ሽግግር አቅም በማሳደግና ወጭ በመቀነስ የሥልጠና ጥራትን ለማስጠበቅና የአገልግሎት አሠጣጥን ለማዘመን ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።

ለድጋፉ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና ያቀረቡት የኮሌጁ ዲን ኮሌጁ የቁሳቁስ ዝርጋታ ስራው በቶሎ እንዲጠናቀቅና ወደ ትግበራ እንዲገባ በትኩረት እንደሚሰራ የዞኑ መንግስት ኮምኒዩኬሽን ጉዳዮች መምሪያ መረጃ ያላክታል።

የታርጫ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ላለፉት አመታት በርካታ ሰልጣኞችን በተለያዩ የሙያ መስኮች በማስልጠን ወደ ስራ እያስገባ የሚገኝ አንጋፋ ኮሌጅ መሆኑ ይታወቃል።