ሚኒስቴሩ ለአፋር ክልል ከ54 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ሚያዝያ 21/2014 (ዋልታ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በአፋር ክልል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ተቋማት ከ54 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉ 307 ማሽነሪዎች፣ 10 ሺሕ 79 የእጅ መሳሪያዎች፣ 3 ሺሕ 828 የተለያዩ ቁሳቁስና የሥልጠና ግብዓቶች በዓይነት እና በገንዘብ አበርክቷል።

ድጋፉን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ለአፋር ክልል ርዕሠ መሥተዳድር አወል አርባ ሰመራ በመገኘት አስረክበዋል፡፡

አሸባሪው በአማራ እና አፋር ክልሎች በፈፀመው ወረራና በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ከተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር በርካታ መሰረተ-ልማቶችና ተቋማት ሲወድሙ፣ ቀላል የማይባሉት መዘረፋቸው ይታወሳል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች ጣቢያዎች ይገኙበታል፡፡

በክልሉ አራት ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ሦስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና 119 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የወደሙ ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ዜጎች ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በዚህም ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር በዘርፉ የክልል ቢሮዎችን፣ ኮሌጆችን፣ ተጠሪ ተቋማትንና አጋር አካላትን በማስተባበር 1 ሺሕ 812 ማሽነሪዎችን፣ 24 ሺሕ 039 የእጅ መሳሪያዎችን፣ 4 ሺሕ 296 ቁሳቁሶችን፣ 8 ሺሕ 580 የስልጠና ግብዓቶችን፣ 6 ሺሕ 157 የተለያዩ የቢሮ ዕቃዎችን ማሰባሰብ ተችሏል፡፡

ለስልጠና ማስጀመሪያ እንዲሆን የተሰባሰበው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን 223 ሚሊየን 482 ሺሕ ብር በላይ እንደሚገመት የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

በተመሳሳይም ሚኒስቴሩ በትላንትናው ዕለት በአማራ ክልል በሽብር ቡድኑ ጉዳት ለደረሰባቸው የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ኢንተርፕራይዞች መልሶ ግንባታ ከ187 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የገንዘብና ዓይነት ድጋፍ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡