ሚኒስቴሩ ሥራቸውን በአግባቡ በማይወጡ የሲሚንቶ አከፋፋዮችና አምራቾች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ

ሰኔ 1/2014 (ዋልታ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሥራቸውን በአግባቡ በማይወጡ የሲሚንቶ አከፋፋዮችና አምራቾች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከ230 በላይ የሲሚንቶ አምራቾችና አከፋፋዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

ውይይቱን የመሩት በሚኒስቴሩ የንግድ ሥርዓትና ላይሰንሲንግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ሃሰን ሙሃመድ በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ጉዳይ ሀገራዊ ችግር እንደሆነና ለዚህም ችግር መከሰት የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረትን ተከትሎ የግብይት ሥርዓት ላይ የሚስተዋለው ውስብስብ ችግር የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል፡፡

የግብይት ሂደቱን ውስብስብ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ እና ዋንኛው የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም አለማደግ እና በግብይት ሂደቱ ውስጥ ምንም እሴት የማይጨምሩ የህገ ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት ሲሆን በቅድሚያ ገንዘብ በመሰብሰብ ቅድመ ሽያጭ መፈፀም፣ ፋብሪካዎችና አከፋፋዮች የሽያጭ ዋጋ በራሳቸው ተመን የማውጣት ተግዳሮቶች ላይ ግምገማ ተካሂዷል።

በሚኒስቴሩ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ግዛው ተክሌ በበኩላቸው ምንም እንኳን ሥራቸውን በጥሩ ሥነምግባር እያከናወኑ ያሉ አከፋፋዮች ቢኖሩም ይህንን የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የግላቸውን ኪስ ለማድለብ በቀጥታ ከፋብሪካ የተረከቡትን ምርት በተጋነነ ዋጋ በመሸጥ የግብይት ሰንሰለቱን የሚያዛቡና የሀገርን ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ አከፋፋዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥት የሲሚንቶ ምርት ዋጋ ላይ የቁጥጥር ሥርዓት ማንሳቱን ተከትሎ በፊት ሲሸጥ ከነበረበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጭማሪ በማድረግ በአሁኑ ወቅት ሲሚንቶ በገበያ ላይ እስከ 1200 ብር እየተሸጠ መሆኑን የጠቀሱት አማካሪው ይህም ያልተገባ ድርጊት መንግሥት ካሁን ቀደም በሲሚንቶ የግብይት ሂደት ውስጥ ያስቀረውን የዋጋ ቁጥጥር ሥርዓት በድጋሜ እጁን እንዲያስገባ እያስገደደው ይገኛልም ብለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የዜጎችን ሠላማዊ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴን የማስጠበቅ ግዴታ ስላለበት በነዚህ ሕገ ወጥ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ሥርዓት አልበኝነትን ለመከላከል ያመች ዘንድ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከአምራቾች፣ ከአከፋፋዮች እና ከሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ማኅበራት የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡

ኮሚቴውም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሲሚንቶ ምርትና ምርታማነት እና ግብይት ዙሪያ የሚስተዋሉ መሠረታዊ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ እርምጃ በማመላከት ለሚኒስቴሩ እንዲያቀርብ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የሲሚንቶ አምራቾችና አቅራቢዎችም መንግሥት ሙሉ በሙሉ ግብይቱን እንዲቆጣጠር ጠይቀው በቁጥጥሩ ለመመራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ስምምነት ላይ መደረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርቶ የተገኘ የሲሚንቶ አምራች፣ አከፋፋይ እና ቸርቻሪ ነጋዴ ላይ እስከ ንግድ ፈቃድ እገዳና ስረዛ የሚደርስ እንዲሁም እንደጥፋቱ ስፋትና ክብደት ሌሎች ሕጋዊ እርምጃዎችም እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW