ሚኒስቴሩ በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ

ሚያዚያ 28/2014 (ዋልታ) የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የህጻናት አድን ድርጅት ዩኔሴፍ ጋር በመተባበር በጎዴ ዞን በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ቁሳቁሶችና 2 ሚሊዮን 34 ሺህ 425 የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

ከዩኒሴፍ በኩል የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ለአስር ሺህ አባወራዎች በቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ፣ የድርቅና የጎርፍ አደጋዎችን ተከትሎ ለሚከሰቱ የሰብአዊ ቀውሶች መከላከያ፤ የህጻናት ደህንነት ከለላን ለማጠናከርና ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዚሁ ሰብአዊ አገልግሎት የሚውል የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ በተለይም ለህጻናትና እናቶች የአልሚ ምግብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በድርቁ ምክንያት የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉበትን ሁኔታ ለመለየትና ችግሮቻቸውን በቀጣይ በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል ግብአት ለማግኘት ጉብኝትና ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱ ላይ በድርቁ ምክንያት የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እስካሁን ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይ ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የተነሱትን ጥያቄዎች ተገቢነታቸውን በመውሰድ ከክልሉ መንግስትና ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰራ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የክልልና የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ መገኘታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል::