ሚኒስቴሩ ትግራይ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አጓጉዟል

ነሀሴ 07/2013 (ዋልታ) – የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትግራይ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች 10 ሺህ 164 ተማሪዎችን ማጓጓዙን አስታወቀ።
ተማሪዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት በጉዞ የባከነባቸው የእረፍት ጊዜ እንደሚካካስላቸውም ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ ተማሪዎቹን እስከ ነሃሴ 6 ባለው ጊዜ ከፌደራልና አፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች እንዲሁም ከትራንስፖርት ማህበራት ጋር በመተባበር በሰመራ ዩኒቨርሲቲ በኩል እስከ ኮምቦልቻና አዲስአበባ ድረስ ማጓጓዝ ተችሏል፡፡
ተማሪዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት በጉዞ የባከነባቸው የእረፍት ጊዜ እንደሚካካስላቸው የገለፀው ሚኒስቴሩ፤ ተማሪዎች ክረምቱን በበጎፍቃድ ስራ እዲያሳልፉ አሳስቧል፡፡
አስፈላጊ መረጃዎችንም ከሚኒስቴሩ ድረገፅና ማህበራዊ ትስስር ገፅ ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁሟል።
የ2013 ዓም ይመረቁ የነበሩ ተማሪዎች እና ያልተጠናቀቀ የትምህርት ተግባር ያላቸው ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበትና የሚመረቁበትን ሁኔታ እንሚያመቻች ሚኒስቴሩ ለኢዜአ ገልጿል።
የክረምት ተከታታይ ትምህርት ያላቸው እና በፀጥታ ችግር ወደቦታው መሄድ ያልቻሉ በቀጣይ በሚቀመጥ አቅጣጫ መሰረት ትምህርት የመከታተል እድል ይመቻቻል ብሏል፡፡