ሚኒስቴሩ ከተጠሪ ተቋማት ጋር ዓለም ዐቀፍ የሴቶች ቀንን አከበረ

የካቲት 30/2014 (ዋልታ) የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዓለም ዐቀፍ የሴቶች ቀንን አከበረ።

በመርኃግብሩ በኢትዮጵያ ታሪክ ታላላቅ ጀብድ የሰሩ፣ በስፖርቱም ዘርፍ ታሪክ ያኖሩ ሴቶች ተወስተውበታል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ኢትዮጵያ በርካታ ታላላቅ ሴቶችን ያፈራችና ዓለም እንደ መልካም ተሞክሮ ብዙ ሊማርባት የምትችል አገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

የሴቶች፣ ህፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ወይንሸት ኃ/ማርያም በኢትዮጵያ ለ46ኛ ጊዜ “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ሃሳብ የሴቶች ቀን ሲከበር ወሩ የአድዋ ድል የተከበረበት ሴቶች በጀግንነት እና ታላቅነት ታሪክ የሰሩበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በመርኃግብሩ የተለያዩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን “ሴቶች እና ንባብ” በሚል ርዕስ ውይይት ተካሂዷል።

በቁምነገር አሕመድ