ሚኒስቴሩ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የነዳጅ ድጎማን ለታለመለት ዓላማ ለማዋል እና የመሠረተ ልማት ደህንነት ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

በስምምነት ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ አገልግሎቱን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲከውን ለማስቻል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ድጋፍ ወሳኝ ነው፡፡

የፌዴራል ፖሊስ በመንገድ ደህንነት፣ በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር ደህንነት፣ በአቪዬሸን ዘርፍ ከክልል የፖሊስ መዋቅር ጋር በመሆን ሀገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ስምምነቱ የነዳጅ ድጎማ በተቀመጠለት ታሪፍ ተግባራዊ እንዲሆን እና የፌዴራል ፖሊስ ባሉት አደረጃጀቶች በመታገዝ ቁጥጥርና ድጋፍ የሚያደርግበትን እድል የሚፈጥር ነውም ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው የፖሊስ ኮሚሽኑ ዋነኛ ስራ የዜጎችን ሰላምና ደህንነትን እንዲሁም የሀገርን ሃብት ከጉዳት መጠበቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ስምምነቱ የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ እንደሚያግዝ ገልጸውየነዳጅ ድጎማ ስርዓት ሀገርንም ህዝብንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መናገራቸውን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡