ሚኒስቴሩ የማዕድን ዘርፉን ለማሳደግ ከዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር መስራት ያስፈልገናል አለ

ግንቦት 2/2014 (ዋልታ) የማዕድን ዘርፉን ለማሳደግ ከዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ መስራት እንደሚስፈልግ የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡

የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝ ለማድረግ ከዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መምከራቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የጂኦተርማል የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በፋይናንስ ለመደገፍ ከተቋማቱ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የማዕድን ዘርፉ ከወቅቱ የዓለም ሁኔታ ጋር እንዲራመድና ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲያድግ ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጋር መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።

በጉዳዩ ዙርያ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከኔዘርላንድ ልማት ባንክና ከፈረንሳይ ልማት ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቁመው፤ የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝ ከስምምነት መደረሱንም ገልጸዋል፡፡