ሚኒስቴሩ የጥምቀትና ገና በዓልን በድምቀት ለማክበር የተለያዩ መርሃግብሮች ማሰናዳቱን ገለፀ

ታኅሣሥ 23/2014 (ዋልታ) የቱሪዝም ሚኒስቴር የጥምቀትና የገና በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችሉ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ማሰናዳቱን አስታወቀ።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የቱሪዝሙን ዘርፍ ብሎም የአገርን ምጣኔሃብት ለማነቃቃት የተለያዩ ሥራዎች እየተከወኑ ነው ብለዋል።

የመንግሥትን ወደ አገር ቤት ግቡ ጥሪን ተከትሎ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እየገቡ ነው፡፡

በዚህም ዲያስፖራው አመቺ ቦታ ላይ በመሄድ በዓሉን እንዲያከብርና የክልል ከተሞችንም እንዲጎበኝ ጥሪ ቀርቧል።

ከጥር 1 እስከ 6 የቱሪዝም ምርቶች የሚተዋወቁበት የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚቃኙበት ሁነት መዘጋጀቱ ተገልጿል።

ከጥር 4 እስከ 7 ክልሎች ያላቸውን ባህልና እሴት እንዲሁም ልዩ ሃብት የሚያሳዩበት መርሃ ግብር ላይም ዲያስፖራዎች እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

በሽብርተኛው ትሕነግ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉም ተነግሯል።