መስከረም 4/2015 (ዋልታ) የውጭ ጉዳይ እና የገንዘብ ሚኒስቴሮች ከዲያስፖራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለአንድ ወር የሚቆይ ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች የሚውል አለምአቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ አስጀምረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የዲያስፖራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄነራል መሀመድ ኢድሪስ እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች በትናትናው እለት በበይነ መረብ በኩል በተደረገው የማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተዋል።
በመረሃ-ግብሩ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዋ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በሁሉም ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄውን እንዲቀላቀሉ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ባለፈው በጀት አመት በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ የተመዘገቡ ስኬቶች እና ክፍተቶች የተዳሰሱ ሲሆን በተለይ ለሀገራዊ ጉዳዮች ቴክኖሎጂን የመጠቀም ልምድ እንደ ጉልህ ጥንካሬ ተነስቷል።
አምባሳደር ብርቱካን በሁሉም ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ሚሲዮኖች ውስጥ የተደራጁ የገቢ አሰባሳቢ አስተባባሪዎች ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ አባላት እና ከኢትዮጵያ ወዳጆች ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንዲሁም ለገቢ ማሰባሰቢያ ምቹ የሆኑ አሰራሮችን በመተግበር የገቢ ማሰባሰብ ስራው እንዲቀላጠፍ የበከሉላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።