ሚኒስትሩ ለቀጣይ 5 ዓመታት የሚበቃ የጨው ምርት እንዳለ አስታወቀ

ነሀሴ 24/2013 (ዋልታ) – የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአፍዴራ የኢትዮጵያን ህዝብ ለቀጣይ 5 ዓመታት ሊመግብ የሚችል የምግብ ጨው ክምችት መኖሩን አስታወቀ፡፡

ሰሞኑን ተፈጥሮ የነበረው የጨው ዋጋ መጨመር ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡

አፍዴራ ላይ ጨው ወደ መኪና ላይ በሚጭኑ ማህበራት የመጫኛ ዋጋ ይጨመርልን ጥያቄ በማንሳታቸው ጨው አምራች እና ጨው ወደ መኪና ላይ በሚጭኑ ማህበራት መካከል ጊዜያዊ አለመግባበት ተፈጥሮ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ  ጨው ለአንድ ወር ሳይጫን በመቅረቱ ምክንያት በገበያ ውስጥ የጨው ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ እንደነበር ሚኒስቴሩ ጠቁሟል፡፡

ሆኖም በአምራቾቹና በጫኞቹ መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት የተፈታ በመሆኑ በቂ የጨው ምርት ወደ ገበያ እየቀረበ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት አፍዴራ ላይ 30 ሚሊየን ኩንታል የጨው ክምችት  መኖሩን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

የሀገሪቱ ወርሃዊ የጨው ፍጆታ 500 ሺህ ኩንታል መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ በአፍዴራ የሚገኘው የጨው ክምችትም ለቀጣይ 5 ዓመታት ፍጆታ የሚበቃ መሆኑን አመላክቷል፡፡

አሁን ላይ በሀገሪቱ 6 ህጋዊ  ጨው አምራች ፋብሪካዎች መኖራቸውን ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡