ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ከእስራዔል አምባሳደር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

ሐምሌ 21/2013 (ዋልታ) የሥራ እና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ ከእስራዔል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሯ ውይይቱን አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እስራዔል በርካታ ውጤታማ የንግድ ሥራዎች ያሉባት፣ የዓለማችን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እና ለቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎች ምቹ ምኅዳር ያላት ናት ብለዋል፡፡

እስራዔል በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አልፋ በከፍተኛ መጠን የሥራአጥ ቁጥሯ ዝቅ እንዲል ማድረጓንም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ይህን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እንዲሁም በክኅሎት ልማት የግሉን ዘርፍ በባለቤትነት ያሳተፉበትን አግባብ ብሎም ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራዎች ምቹ ምኅዳር በመፍጠር የዓለማችን ቀዳሚ ሀገር የሆነችበትን ሚስጥር ለኢትዮጵያ ለማካፈል እስራዔል ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደሩ መናገራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም እስራዔል በሥራ ባሕል፣ በሙያ ደኅንነትና ጤንነት ላይ ያላትን ልምድ እንደምታካፍል እና በአጫጭርና በረዥም ጊዜ ሥልጠናዎች በኢትዮጵያ ያለውን የሰው ኃይል ለማብቃት እንደምትሠራ ያላትን ቁርጠኝነት ማረጋገጧን ገልጸዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራትም ከቀደሙት የሚጠቅሙ ምርጥ ልምዶችን ወስደው ችግሮቻቸውን መፍታትና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ምርጥ ልምዶች እና ተሞክሮዎች በመውሰድ ችግሮችን ለመፍታትና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል፡፡