ግንቦት 17/2013 (ዋልታ) – የደቡብ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን መሠረታዊ የሰራተኞች ማህበር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የ2 ሚሊየን 485 ሺህ ብር ቦንድ ግዢ ፈፀመ።
የማህበሩ አመራሮች የቦንድ ግዥ የተፈፀመበትን ቼክ ሰራተኞችና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀዋሳ ቅርንጫፍ አስረክቧል።
በርክክቡ ሥነ ሥርዓት የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ሸጉ ማናዬ እንዳሉት፤ ማህበሩ የቦንድ ግዥውን የፈጸመው ከሰራተኞች መዋጮና ከተለያዩ ገቢዎች ከሰበሰበው ተቀማጭ ላይ በመቀነስ ነው።
ማህበሩ እስካሁን ከ430 በላይ አባላቱን በእጣ በመለየት በሁለት ዙር የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ሂደት በሥፍራው ተገኝተው እንዲጎበኙ ማድረጉን ጠቁመው፣ ይህም ሰራተኛው ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናከር ማነሳሳቱን አስታውቀዋል።
የባለሥልጣኑ ሰራተኞች እስካሁን ለሶስተኛ ጊዜ በአንድ ወር ደሞዛቸው ቦንድ መግዛታቸውን የጠቆሙት አቶ ሸጉ፣ አሁን ደግሞ የማህበሩ አባል የሆኑ 1 ሺህ 402 ሰራተኞች ከወር ደመወዛቸው በመቀነስ የ2 ሚሊየን 485 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውቀዋል።
የውስጥና የውጭ ጠላቶች የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎልና ሁለተኛ ዙር የውሀ ሙሌት እናዳይከናወን ጥረት እደረጉ በመሆናቸው በቁጭት በመነሳሳት ቦንድ ለመግዛት መወሰናቸውን አስረድተዋል።
ከማህበሩ አባላት መካከል ወይዘሮ እልፍነሽ ከበደ በሰጡት አስተያየት፤ ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ መድረሱና ሁለተኛ ዙር የውሀ ሙሌት ለመጀመር መቃረቡ ለእኛ ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።
ይህ እውን እናዳይሆን የውጭ ኃይሎች ጫና እየፈጠሩ እንደሚገኙ አስታውሰው በዚህ ወቅት ከመንግስት ጎን መቆማችንን ለማሳየት ቦንድ ለመግዛት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ሰራተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ዘገየ ኃይለስላሴ፣ በአሁን ወቅት የዓለምን ትኩረት የሳበው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው እንዲጓተት የሚፈልጉ አካላት እርስ በእርሳችን እንድንከፋፈል ተግተው እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
የማህበሩ አባላት ያደረጉት ድጋፍ ለሀገር ያላቸውን ተቆርቋሪነት በተግባር ያሳዩበት እንደሆነም ገልጸዋል።
ይህ ተግባር የግድቡን ግንባታ ሌት ተቀን ተግተው እየሰሩ ለሚገኙት ሰራተኞችም ትልቅ ማበረታቻ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚኪያስ እስራኤል በበኩላቸው፣ የህዳሴው ግድብ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ የሉአላዊነታችን ተምሳሌትና የመፃኢ እድላችን በር ከፋች ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
እስካሁን የኢትዮጵያ ህዝብ እያሳየ ያለው ድጋፍም ተባብረን ከተነሳን ካሰብንበት ለመድረስ ሊያስቆመን የሚችል ኃይል እንደሌለ ማሳያ ነው ያሉት ኃላፊው፣ የግድቡ ግንባታ ለፍፃሜ እስከሚደርስ ድረስ የተጀመረው ትብብር ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።