ማህበሩ ለአርሶ አደሩ የሚያቀርባቸው የፀረ አረም ኬሚካልና አካንቶ ፕላስ የዋግ መከላከያዎች ውጤታማ መሆናቸው ተገለጸ

ጥቅምት 01/2014 (ዋልታ) ኬምቴክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለአርሶ አደሩ የሚያቀርባቸው ፓላስ ሱፐር የፀረ አረም ኬሚካልና አካንቶ ፕላስ የዋግ መከላከያዎች ውጤታማ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

ማህበሩ በምስራቅ ጎጃም ሁለት እጁ እነብሴ ወረዳ የአርሶ አደር ማሳ ላይ ባስጀመረው ሙከራ የኬሚካሎቹ ውጤታማነት ከእስካሁኖቹ ምርቶች የተለዩ እንደሆነ በግብርና ባለሙያዎች ጠቁሟል፡፡

በሰብል ምርት ግብርና ውስጥ የአርሶ አደሩ ፈታኙ ስራ አረም ሲሆን፣ ከሰብል ቡቃያ ጋር አብሮ የሚያድግ አረም የተባለ ተክል ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብን  በመጨረስ የአርሶ አደሩን  ድካም መና የሚያስቀር ነው፡፡

አረሙ በሰብሉ ውስጥ በአግባቡ ካልታረመ በአንድ ሄክታር ላይ ከሚገኘው ምርት ውስጥ እስከ 30 በመቶ የምርት ቅናሽ ይፈጥራል ነው የሚባለው፡፡ ይህንን አረም የሚያጠፉ ኬሚካሎች ገበያውን እየተቀላቀሉ ቢሆንም፤ ውጤታማ የሚባሉት ጥቂት መሆናቸው በባለሙያዎች ይጠቀሳል፡፡

ይሁን እንጂ ኬምቴክስ ለአርሶ አደሮች ይዞ የመጣው የፀረ-አረም ኬሚካሎች ውጤታማነታቸው በሰብል ማሳዎች ላይ እየታየ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ድርጅቱ በምስራቅ ጎጃም ሁለት እጅ እነሴ ወረዳ 8 ሄክታር መሬት ላይ በራሱ ባለሙያዎች ያለምንም ክፍያ የፓላስ ሱፐር የፀረ-አረምና አካንቶ ፕላስ የዋግ ኬሚካሎች እርጭት አድርጓል፡፡ ይህም አርሶአደሮችን እንዳገዛቸውና በሰብላቸው ላይ ለውጥ እያዩ መሆኑን ለዋልታ ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

ኬምቴክስ ለአረሶ አደሩ ያቀረበው የፓላስ ሱፐር የፀረ አረም ኬሚካል ወጤታማ መሆኑን የሚናገሩት የግብርና ባለሙያዎች፣ የአርሶ አደሩ ምርታማነትም ተያይዞ እንደሚጨምር አክለዋል፡፡ ለማሳያነት የተጀመረው ተሞክሮም ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች እንደሚሰፋ ነው የተነገረው፡፡

በምስራቅ ጎጃም ሁለት እጅ እነሴ ወረዳ በ2013/14 የምርት ዘመን 35 ሺሕ 814 ሄክታር መሬት በሰብል የተሸፈነ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1.2 ሚሊዮን ኩንታል ምርትን ለመሰብሰብ እንደ ፓላስ ሱፐር አይነት የግብርና ግብአትና ሌሎች ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛል፡፡

በደምሰው በነበሩ