ማኅበራቱ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ደብዳቤ ጻፉ

ሰኔ 1/2014 (ዋልታ) አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተቋቋሙ ዘጠኝ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንና አባል ሀገራት የተቃውሞ ደብዳቤ ጻፉ።

ማኅበራቱ ደብዳቤውን የጻፉት በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት ኢትዮጵያ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ተቋማቶቿ አማካኝነት እያከናወነች ያለውን አበረታች ተግባራት መደገፍና ማገዝ ሲገባው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በሚጣረስና በአንዲት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነትን በሚያሳይ መልኩ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽኑ የኢትዮጵያን ጉዳይ እንዲያይ ያቋቋመውን አዲስ አሰራር በመቃወም ነው።

ማኅበራቱ ከዚህ በፊት የቀረቡ ክሶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ የወታደራዊ ችሎት፣ የፌዴራልና የክልል ፖሊስ አቃቤ ሕጎች በገለልተኝነት ምርመራዎችን በማድረግ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በትግራይ፣ በአማራና አፋር ክልሎች ተፈጽመዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶችን በመመርመር አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

ይህም መንግሥት ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                               በመጪው ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም አባል ሀገራት በጄኔቫ ለ50ኛው የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በሚሰበሰቡበት ወቅት ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ክሶችን ለማጣራትና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ እያከናወነችው ያለውን ተግባር ከግምት ውስጥ በማስገባት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተቋቋመውን ዓለም ዐቀፍ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የባለሙያዎች ቡድንን እንዲያፈርሱ አሳስበዋል፡፡

በተጨማም ቡድኑ እንዲጠቀምበት የተያዘውን በጀት ኢትዮጵያ በዘርፉ ለምታከናውነው ሥራ አቅም መገንቢያ እንዲመደብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።