ማዕከሉ 4 የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ለማሽን የማስተማር ስራ እየሰራ ነው

ሚያዝያ 07/2013 (ዋልታ) – አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛና ትግሪኛ ቋንቋዎችን ለማሽን የማስተማር ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል  ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀነስ ማዕከል ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ያዘጋጁት “የሰው ሰራሽ አስተውህሎ ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያው አውደ ጥናትና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል በፋይናንስ፣ በትራንስፖርት፣ በጤና፣ በቋንቋ በግብርና በሌሎች ዘርፎች የሰራቸውና እየሰራቸው ያሉ ስራዎች በአውደ ጥናቱና አውደ ርዕዩ ቀርበዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብረሃም በላይ (ፒ ኤች ዲ) የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ ገና አዲስ የተቋቋመ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በብዙ ዘርፎች አበረታች ውጤቶችን እያሰመዘገበ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ለቴክኖሎጂው ስርፀት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር እንጂነር ወርቁ ጋቸና  የሀገራችን ቋንቋዎች ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ በሰው ሰራሽ አስተውህሎ ለማሽን የማስተማር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን ዘመኑ በደረሰበት በሰው ሰራሽ አስተውህሎ በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ማለታቸውን  ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሰው ሰራሽ አስተውህሎ ማሽኖች ሰው ሰራሽ የማሰብ ችሎታ እንዲኖራቸው በማድረግ ካለሰዎች እርዳታ ራሳቸውን ችለው ስራዎችን እንዲሰሩ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል የሰው ሰራሽ አስተውህሎ ቴክኖሎጂን በኢትዮጵያ እንዲመራና እንዲደግፍ ሃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው።