ማዕከሉ 5 አዳዲስ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን አስመረቀ

ሐምሌ 23/2013 (ዋልታ) – ኦርቢት የኢኖቬሽን ማጎልበቻ ማዕከል አምስት አዳዲስ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን አስመረቀ፡፡

ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶቹ የተሰማሩት በጤና፣ ትምህርትና አገልግሎት ዘርፍ ላሉ ችግሮች የቴክኖሎጂ መፍትሄ መስጠት ላይ ነው።

በኢኖቬሽን ማጎልበቻ ማዕከሉ 120 ሃሳቦች ተመዝግበው ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ የማበልፀግ ስራ ተሰርቶላቸዋል።

ከ15ቱ መካከል 5ቱ ደግሞ በዛሬው እለት ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅት ሆነው ተመርቀዋል።

የኦርቢት መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ፓዚዮን ቸርነት ማዕከሉ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች አቅም ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የስራ እድል፣ ችግርን ለመፍታት በሚደረግ ጥረት ውስጥ እንደሚገኝ ያነሱት ስራ አስኪያጁ ማዕከሉ ከሃሳብ ጀምሮ እስከ ካምፓኒ ምስረታ ድረስ የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ገበያውን ተቀላቅለው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል መንግስት አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የፈጠራ ስራዎች ወደ ተቋም የሚሸጋገሩበት ሰፊ ዕድል እንዲኖር እንፈልጋለን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው መንግሥት የተመረቁትን ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምፀሃይ ጳውሎስ የጤና ስርዓቱን ዲጂታል በማድረግ የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል ብርቱ ስራ እንደሚጠይቅና የጤና ሚኒስቴርም በዚህ ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሜዲኬት፣ ጤና፣ ተማሪቤት፣ ገበታና ነርድ በዛሬው እለት የተመረቁ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች መሆናቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።