ማዕድ ማጋራትና የበዓል ስጦታ

ጳጉሜ 3/2013 (ዋልታ) የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የወጣቶች እና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የ2013 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማዕድ ማጋራትና የበዓል ስጦታ ማበርከት መርሃ ግብርን አከናወነ።

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኤሊያስ መሀመድ ባለፉት 3 ወራት በተከናወነ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤት እድሳትን ጨምሮ በዓይነት ለአቅመ ደካሞች ወደ 32 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በዛሬው እለት ብቻ ለ8 ሺሕ አቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ የምግብ ዘይት፣ በግ፣ ዶሮ የመሳሰሉ የዓይነት ድጋፍን ያደረገ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ከኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ጋር በተገናኘ ለ750 አቅመ ደካሞች ብቻ ርክክብ ተደርጓል።

ለቀሩት ድጋፉ በየቤታቸው ተደራሽ እንደሚደረግ የተገለፀ ሲሆን በአጠቃላይ ለአዲሱ ዓመት 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ ለአቅመ ደካሞች ተደርጓል ተብሏል፡፡

በደረሰ አማረ