ምርት ገበያው የማዕድንና የቅመማ ቅመም ምርቶችን ማገበያየት ሊጀምር ነው

ሐምሌ 28/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የማዕድንና የቅመማ ቅመም ምርቶችን ወደ ግብይት ስርዓት ውስጥ ሊያስገባ መሆኑን አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ግብይት ስርዓት ለማስገባት የአዋጪነት ጥናት እንደሚያደርግ ገልጿል።

ከ13 ዓመት በፊት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በቆሎና ስንዴ በማገበያየት ነበር ስራውን የጀመረው።

በሁለት የግብርና ምርቶች የጀመረውን ግብይት አሁን ወደ 13 በማሳደግ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን እያገበያየ ይገኛል።

የምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ስራ አስኪያጅ ነጻነት ተስፋዬ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ከግብርና ምርቶች ውጪ የማዕድን ምርቶችን ማገበያየት ይጀመራል።

ኦፓል፣ ሳፋየርና ኤመራልድ የጌጣጌጥ ማዕድናት ወደ ግብይት ስርዓት ውስጥ እንደሚገቡና በቀጣይ ሌሎች የማዕድን ምርቶች የማገበያየት እቅድ እንዳለ ገልጸዋል።

የማዕድን ምርቶች በምርት ገበያው እንዲገበያዩ መደረጉ ሕጋዊ ስርዓትን የተከተለ ግብይት በመፈጸም ሕገ-ወጥ የማዕድን ሽያጭ ለማስቀረት እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የስራ እድል ከመፍጠርና ምርት ገበያው ምርቶችን የማገበያየት አቅሙን ለማሳደግ እድል ይፈጥርለታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የማዕድን ምርቶችን በምርት ገበያው እንዲገበያይ የሚያስችለው ስምምነት መፈራረሙ የሚታወስ ነው።

የሁለቱ ተቋማት ባለሙያዎች ምርቶቹን ማገበያየት የሚያስችል የገበያ ስርዓት ደንብ እያዘጋጁ እንደሚገኝና በማዕድን ዘርፍ ያሉ ባለድርሻዎች ያሳተፈ የኢንዱስትሪ ምክክር መድረክ ተካሄዷል።

በኢንዱስትሪ ምክክር መድረኩ የተነሱ ምክረ ሀሳቦችን  በመመርኮዝ ምርት ገበያው ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝም ነው ስራ አስኪያጁ ያስረዱት።

ምርት ገበያው በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ከማዕድን ምርቶች በተጨማሪ የቅመማ ቅመም ምርቶችን ወደ ግብይት ስርዓቱ ያስገባል ብለዋል።

በዚህም ጥቁር አዝሙድ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ እርድ፣ ኮረሪማና አብሽ እንዲሁም ከቅመማ ቅመሞች በተጨማሪ ጓያ፣ የዱባ ፍሬ፣ ሙጫ፣ ኦቾሎኒና ሩዝ ወደ ግብይት ስርዓቱ ይገባሉ።

ወደ ግብይት ስርዓት ውስጥ የሚገቡት ምርቶች በወጪ ንግዱ የሚያስፈልገውን የምርት መጠን ለማሳደግ እንዲሁም አርሶ አደሩና አምራቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች የማቅረብ አስተሳሰባቸውን እንዲያሳድጉ አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት አቶ ነጻነት።

በሌላ በኩል ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ በምርት ገበያ ስርዓት ውስጥ ተግዳሮት ከሆኑ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በምርት ገበያው የሚገበያዩ ምርቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት አገራት በማስገባት እየተሸጡ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ሕገ-ወጥ ተግባራቱ የወጪ ንግድ ላይ የሚገኘውን ገቢና በሕጋዊ የግብይት ስርዓት ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻዎች ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት ምርት ገበያው ጉምሩክ ኮሚሽንን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሳራ መሆኑን አመልክተዋል።

ሕገ-ወጥ የምርት ንግድና ኮንትሮባንድ ለመከላከል የክትትልና የቁጥጥር አድማስን መፍጠርና የግንዛቤ  ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

በጸጥታ ችግር ምክንያት በግብይት ላይ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር ምርት ገበያ ካለው የምርት ክምችት እያቀረበ ይገኛልም ብለዋል።

የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማዕከላትን ማስፋት፣ተጨማሪ ቅርንጫፎችን መክፈት፣ የምርት ማከማቻ መጋዘኖችን ቁጥር ማሳደግና ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርበውን የምርት መጠን ማሳደግ በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት አክለዋል።

በ2013 በጀት ዓመት የርግብ አተር፣ ዥንጉርጉር ቦሎቄና ፒንቶ ቢን ወደ ግብይት ስርዓቱ መግባታቸውን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በ2001 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሻጮችና ገዢዎችን በዘመናዊ የግብይት ዘዴ የማገበያየት ስራ የሚያከናውን ተቋም ነው።

ምርት ገበያው ሰሊጥ፣ አረንጓዴ ማሾ፣ ቡና፣ ኑግና ቦሎቄ ከሚያገበያያቸው የግብርና ምርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።